ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጀምረን የማንጨርሰው ተናግረን የማንፈጽው ነገር እንደሌለ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ12.74 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነውን ከአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል-ጎሮ-ቪአይፒ ኤርፖርት የተገነባውን አዲስ የኮሪደር ልማት ከጎበኙ በኋላ ልማቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ አራት ኮሪደሮች መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ስምንት ኮሪደሮችን ጀምረን አራቱን ጨርሰናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከአዲስ ኮንቬሽን ማዕከል ጎሮ ቪአይፒ ኤርፖርት የተገነባውን አዲስ የኮሪደር ልማት በውስጡ ዘመናዊ የመንገድ ልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የመኪና መቆሚያ ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ የኮሪደር ልማት ለየት ባለ መልኩ በስፋት በመንገድ ዳርቻዎች በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የማንሰራራት ዘመን በገጠርም በከተማም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሰራናቸው ሥራዎች በርካታ ልምዶችን አግኝተናል፤ ይህ ደግሞ ለቀጣይ ሥራዎች የሚያነሳሳን ነው ብለዋል፡፡
ልማቱ በተለያዩ የአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ እየሆነች መምጣቷን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ያለንን ሀብት ሳናባክን በአግባቡ በመጠቀማችን የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች በጊዜ ለመጨረስ አስችሎናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በሃብተሚካኤል ክፍሉ
#EBC #ebcdotstream #addisababa