ዛሬ ጠዋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል-ጎሮ-ቪአይፒ ኮሪደር መመልከታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባጋራው ጽሁፍ፤ ይኽ አዲስ የተሠራ ባለሁለት አቅጣጫ መንገድ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን ከሲኤምሲ መንገድ ጋር በማገናኘት በከተማዋ ቁልፍ አካባቢዎች የተሳለጠ ግንኙነት እና የትራፊክ ፍሰት የሚፈጥር ነው ብሏል።
290 ሄክታር በሚሸፍን አካባቢ 12.74 ኪሎሜትር የሚረዝም የኮሪደር ልማት ተሰርቷል፤ የእግረኛ መንገድ ጨምሮ፣ 15.27 ኪሎሜትር የብስክሌት መጋለቢያ ተገንብቷል ሲልም ጽ/ቤቱ ገልጿል።

5 ዘመናዊ የታክሲ እና አውቶቡስ መናኸሪያዎች፣ 4 የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና 17 የመጫኛ እና ማውረጂያ ስፍራዎች በመሠራታቸው ኮሪደሩ የተሽከርካሪ ጭንቅንቆችን በማቅለል የትራንስፖርት ውጤታማነትን እንደሚያሳልጥም አስታውቋል።
በኮሪደሩ በመሬት ሥር የተቀበሩት የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መሥመሮች፣ የውሃ ፍሳሽ መውረጃዎች ብሎም የመንገድ መብራቶች ዘመናዊ መሠረተ ልማት እንዲኖር አድርገዋል ብሏል።
የኮሪደር ሥራው መንገዶችን ብቻ የሚያሻሽል አይደለም ያለው ጽ/ቤ፤ የኑሮ ደረጃንም የተሻለ ያደረገ ነው ሲል አስረድቷል።
አካባቢውን ከመሠረቱ ያሻሻለ የ130 ሄክታር የወንዝ ዳርቻ ልማት መከናወኑንም አመላክቷል።

የተለያዩ ግንባታዎች እንዲኖራቸው የተደረጉ አረንጓዴ ስፍራዎች ተሠርተዋል፤ ከ320 በላይ ሕንፃዎች ታድሰዋል፤ ከባቢውን ድንቅ አድርገዋል ሲልም አክሏል።
ውጤቱ በዐይን የሚታይ ነው ያለው ጽ/ቤቱ፤ 350 አዳዲስ ሱቆች ተገንብተው ሥራ መጀመራቸውን አስታውቋል።
የንግድ እንቅስቃሴ ደምቋል፤ የትራፊክ ጭንቅንቅ አቃሏል፤ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተሻሽሏል ሲልም ጽ/ቤቱ አስፍሯል።
አረንጓዴ ስፍራዎቹ ለነዋሪም ሆነ ለጎብኝ ለዐይንም ለጤናም አስደሳች እና ጠቃሚ ሆነው እንደሚታዩም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።