Search

ሴቶች የ ‘ይቻላል’ መንፈስን አንግበው ከተነሱ ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው ይተርፋሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

እሑድ ነሐሴ 25, 2017 72

ሴቶች ያሳለፉትን ማኅበራዊ ችግሮች ትተው የ‘ይቻላል’ መንፈስን በማንገብ ከተነሱ ከራሳቸው ኑሮ አልፈው ሀገራቸው በኢኮኖሚ መቀየር ይችላሉ ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

በአዲስ አበባ ከተማ በ "ለነገዋ ሴቶች የተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል" ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ የ3ኛ ዙር ሴት ሠልጣኞች ተመርቀዋል።

ሴቶች ባገኙት እና በሠለጠኑት ሙያቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማብቃት የሚሠራው ተቋሙ ዘንድሮም ከ800 በላይ ሴት ሠልጣኞችን በተለያዩ ሙያ አሠልጥኖ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የማዕከሉ ዳይሬክተር ህርጳሳ ጫላ (ዶ/ር) እንደገለጹት ሥልጠናውን የወሰዱ 810 ሴት ሠልጣኞች የማጠናቀቂያ ምዘና በመውሰድ ከ90 ነጥብ በላይ አምጥተው የብቃት ማረጋገጫ ውጤት ተሰጥቷቸው ተመርቀዋል።

ሠልጣኞቹ በከተማ ግብርና፣ በሆቴል ሙያ፣ በኮንትራክሽን፣ በስነውበት፣ በልብስ ስፌት፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ሌሎች ሙያዎች የተመረቁ ሲሆን፣ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥም የሥራ እድል የተመቻቸለቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ቀደም ሲል ከማዕከሉ የተመረቁ ሠልጣኝ ሴቶች በተለያዩ ሙያዎች ተደራጅተው ሥራ በመፍጠር በሚያገኙት ገቢ ሕይወታቸውን እየመሩ፣ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥም የራሳቸውን ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን ተገልጿል።

ሰልጣኝ ሴቶቹ በየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካኝነት ከከተማዋ ሁሉም ወረዳዎች ተመልምለው ወደተቋሙ በመምጣት ዕድሉን ያገኙ ናቸው።

ተመራቂዎቹ የሴቶችን ችግር በመረዳት ማዕከሉን ለመሰረቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቅርበዋል።

በዓሊ ደደፎ

#ebc #ebcdotstream #AddisAbaba