Search

አዲስ አበባ የምታስተናግደዉ ከ20 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚጠበቁበት ጉባኤ

እሑድ ነሐሴ 25, 2017 303

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤው የኢትዮጵያ መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ ያዘጋጁት ነው። ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለዉጥ መፍትሄዎችን ማፋጠን እና የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።

አፍሪካ ለአየር ብክለት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከ4 በመቶ ያነሰ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየጎዳት ትገኛለች፡፡

በአህጉሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የግብርና ምርታማነት እ.ጎ.አ ከ1960ዎቹ ወዲህ በ34 በመቶ ቅናሽ ማሳቱን የፕንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

በየዓመቱ እስከ 5 መቶ ሺህ ሄክታር ደን የሚመነጠር ሲሆን ይህም በረሃማነትን እያስፋፋ ጉዳቱን ውስብስስብ እያደረገው መጥቷል ነው የሚባለው፡፡

የተራዘመ ድርቅ፣ የአንበጣ እና መጤ ተምች ችግሮች፣ የሰብል በሽታ፣ ጎርፍና መሰል አደጋዎች አፍሪካ የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋገጥ አድርገዋታል ተብሏል፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የጉባኤውን ዝግጅት በማስመልከት ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠና ላይ እንደተገለጸው በጉባኤው ለአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡

ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብርና የታዳሽ ሀይል ልማቶች፤ በኬንያ በስፋት እየተሰራበት ያለው የታዳሽ ሀይል ልማት ተሞክሮዎች ይቀርባሉ፡፡

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘውና በዓለም ሁለተኛው ጥቅጥቅ ደን መገኛ የሆነውን የኮንጎ ቤዚንን ለመጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዲሁም በሰሃል በረሃ እየተገበረ የሚገኘውና 100 ሚሊዮን ሄክታር ደንን እንደገና የመመለስ ስራዎችም አፍሪካ በጉባኤው የምታቀርባቸው አፍሪካዊ መፍትሄዎች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አፍሪካን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረጉት ላለው ስራ የፋይናንስ ድጋፍ የመጠየቅና በአንድ ድምጽ አፍሪካዊ ጥሪ የሚቀርብበት ጉባኤ መሆኑ ሲጠበቅ፤ ሀገራት የፋይናንስ ችግሮቻቸውን ለማቃለል የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳብ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡

አፍሪካ በ2030 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚሰራው ስራ የሚያስፈልጋት ገንዘብ 3 ትሪሊዮን ዶለር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን የተገኘው ግን 30 ቢሊዮን ዶላር ወይም የእቅዱን 20 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ታዲያ ቀሪው ገንዘብ በምን መልኩ ይገኝ በሚለው ላይ ጉባኤው የሚመክር ይሆናል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታው ስዩም መኮነን፤ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽና የገንዘብ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ምንጭ የሆነች አህጉር መሆኗን የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል።

አፍሪካውያን ከዚህ ቀደም  ከባቢ አየር በካይ ሀገራን ገንዘብ በቀጥታ ከመጠየቅ ይልቅ አፍሪካዊ መፍትሄዎችን በማጉላት የትብብር መንፈስን ከፍ ማድረግና እነዚህን ስራዎች በሚደግፉበት ዙሪያ ጫና ለማሳደር ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በጉባኤው በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያላትን የመሪነት ሚና በመወጣት የትርክት ለውጥ እንዲመጣ ትሰራለች ብለዋል።

በካይ ሀገራት የገቡትን የፋይናንስ ቃል ኪዳን ተፈጻሚነት ጉዳይ ላይ ድምጿን በማሰማት የአፍሪካን የፍትሐዊነት ጥያቄ እንደምታቀርብ ነው የተናገሩት።

ከጉባኤው በኋላ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ የአዲስ አበባ ድንጋጌ ይፋ እንደሚደረግና ለተፈጻሚነቱ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

እስከ 23 ሺ ተሳታፊ እንደሚታደምበት በሚጠበቀው ጉባኤ እስከ አሁን ባለው መረጃ መሪዎችን ሳይጨምር 21 ሺህ 600 በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ መመዝገባቸውን ነው የጠቆሙት።

በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ መሰረት እንደሚጥል ተናግረዋል።

በእንቻለው አያሌው