በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን በክላስተር እየለማ የሚገኝ ሰብል በኤርትራክተር እና በድሮን የታገዘ የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት እየተከናወነ ይገኛል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ከናሽናል ኤርዌይስ ጋር በመተባበር ለሚያከናውነው የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በአርሲ ዞን፣ ዲገሉና ጢጆ ወረዳ ተካሂዷል።
በኤርትራክተር የሚካሄደው የፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ የአርሶአደሮችን ጫና የሚያቃልል መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሄርጳ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል በሰብል እንክብካቤ የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የፀረ አረም እና የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስቴር 5 ኤርትራክተር ኤ 02 አውሮፕላን አንዱን በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ የገዛ መሆኑን የገለፁት የናሽናል ኤርዌይስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ብሩ፤ ድርጅታቸው የማስተዳደሩን ሥራ በጨረታ በመውሰድ እያከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አንዱ ኤርትራክተር ኤ 02 አውሮፕላን በቀን በአማካኝ 1 ሺህ 200 ሄክታር ሰብል ፀረ ተባይ ኬሚካል መርጨት የሚችል ሲሆን፤ አምስቱ በቀን 6 ሺህ ሄክታር መሸፈን ይችላሉ ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በክልሉ የተካሄደው የፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት ለምርት ጭማሪ ዋነኛ ምክንያት ስለመሆኑ ከኦሮሚያ ክልልና ከፌዴራል መንግሥት ግብረ መልስ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት መሰል ኤርትራክተሮች ከውጪ በኪራይ እየመጡ ሥራውን እንደሚሰሩ ያስታወሱት አቶ ገዛኸኝ፤ የአሁኑ አሠራር የውጪ ምንዛሬን ከማዳን በተጨማሪ ቴክኖሎጂውን በሀገር ውስጥ አቅም ማስተዳደር የተቻለበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ ኢብራሂም ከድር በበኩላቸው ዞኑ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአካባቢውን አምራችነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
በሞላ ዓለማየሁ
#Oromia #Agriculture #AirTractor #Drone #Pesticides #Herbicides