“ቀጣዩ ትውልድ በራሱ ንዋይ ይገነባዋል፤ ጥናቱ በክብር ይቀመጥለት” የሚል ተስፋ አዘል ትንቢት የተነገረለት ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ።
ኢትዮጵያ ዘመን ተሸጋሪ በሆነው የኪነ ህንፃ ጥበቧ በርካታ ቅርሶች ቢኖሯትም፤ ከግንባታ ግብዓት ባሻገር የደም፣ የላብ፣ የዕንባ እና የውኃ ድምር ውጤት የሆነው ይህ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የጨለማው ዘመን ማብቂያ፣ የብርሃን ዓመት ጅማሮ ነው ሲሉ ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) ተናግረዋል።
ቀድሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የነበሩት ዶ/ር ጥላሁን አሁን የአፍሪካ ቀንድ እና መካከለኛው ምሥራቅ ጂኦፖለቲካ ተመራማሪ ናቸው።
በዓባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ዙሪያ "የግብፅና አጋሮቿ ጠላትነት እስከ መቼ?" የሚል መፅሐፍ የፃፉት ዶ/ር ጥላሁን፤ የግድቡ ግንባታ ቢጠናቀቅም ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ግን ቀጣይ ናቸው ሲሉ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልፀዋል።
የግድቡን ድንበር ተሻጋሪ ጠቀሜታ በተመለከተ በኃይል ኤክስፖርት የተጀመረው የኢኮኖሚ ትስስር ወደ ሌላ እንዲያድግ የማድረግ ዲፕሎማሲያዊ የቤት ሥራዎች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
ከዚህ ባሻገር የግድቡን ደህንነት በተጠንቀቅ ለመጠበቅ ሰላሙን ያሰረፀ እና በአንድ የቆመ ህዝብ ልንሆን ይገባል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ከግድቡ በተጨማሪ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ እያደረግናቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች እና ስምምነቶች የሀገራት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርባቸው በጥንቃቄ ማጤን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBC #EBCdotstream #GERD #ሕዳሴግድብ #RenaissanceDam