Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ያከናወኗቸው ተግባራት

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 48

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሐምሌ እና ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያን የተፋጠነ የልማት አጀንዳ እውን ለማደረግ ቁልፍ የሆኑ ስትራቴጂካዊ ውጥኖችን፣ ግዙፍ ሀገራዊ የፕሮጀክት አፈጻጸምን እና የግንባታ ስምምነትን፤ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ ለማቋቋም የተደረገውን ስምምነትን ጨምሮ ተከታታይ ተግባራትን አከናውንዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወሩ ካከናወኗቸው ቀዳሚ ተግባራት መካከል፤ ከብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን አዲስ የተሠራውን ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ የኮሪደር ሥራ ምረቃ ቀዳሚው ነው።
አካባቢው አስደናቂ ለውጥ ያመጡ አዳዲስ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ የተሻሻሉ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ በታዋቂው የእድ ጥበበ ገበያ በሽሮ ሜዳ የተገነቡ የዘመናዊ ሱቆችን ያካተተ ነው። የኮሪደር ልማት ሥራው የሕፃናት መጫወቻዎች፣ ሰፊ የእግር ኳስ ሜዳ እና የተለያዩ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎች የተከናወኑበት ነው። ይኽ ፕሮጀክት አስደናቂ ለውጥ ከተካሄደባቸው የመዲናዋ ክፍሎች አንዱ ነው።
 
 
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከብልጽግና ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የሥራ ሂደትን በጋራ በመሆን ተመልክተዋል።
ይኽ ሥራ አሁን በተያዘው ምዕራፍ በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚዘልቅና 21.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው። ፕሮጀክቱ በጥቂቱ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ ሕዝብ ፕላዛዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ሱቆች እና አምፊቴአትሮች የተካተቱበትም ነው።
በዚሁም ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተለያዩ የአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማትን እንቅስቃሴ እና የደረሱበትን አሁናዊ የማምረት አቅም (Production capacity) በመዘዋወር ተመልክተዋል።
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳኢንደስትሪ ፓርክ በነበራቸው ጉብኝት በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጪያዎችን እያመረቱ መሆኑን ተመልክተው አድንቀዋል።
 
 
ይኽ ሥራ እሴት የተጨመረባቸው እና ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች እና ፖሊሲዎች የሚያሳኩ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የኢንቨስትመንት ስትራቴጂያችን ጋር የተጣጣመ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።
ወደ ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ተጉዘው የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን እና የፕሮጀክት አፈጻጸሞችን መመልከት የቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በአርባምንጭ ከተማ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትን ጨምሮ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በተለይም ደግሞ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ሥራ በመጠነ ርዕዩ ግዙፍ በመሆኑ አርባምንጭ ታላላቅ ጉባኤዎችን እንድታስተናገድ ያስችላታል።
 
 
 
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ከነበረን ምልከታ ሰፋ ብሎ የተከናወነው የኩልፎ ወንዝ ዳርቻ ልማት ለከተማዋ ልዩ መልኮች ተጨማሪ ገጽታ ፈጥሯል ብለዋል።
ወደ አርባምንጭ ጫካ አዳዲስ የመግቢያ መንገዶች የተሠሩ ሲሆን ለተራሮቹ፣ ለውሃው እና ለከባቢው ደኖች መዳረሻ በር ሆነዋል። በዚሁ ተከታታይ የመስክ ጉብኝታቸው እና የልማት ሥራ ምልከታቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአረንጓዴ ልማት ውጤቶችን እንዲሁም አስደናቂ የፍራፍሬ እርሻ ልማት ሥራዎችን ከአርባምንጭ እስከ ወላይታ ሶዶ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወላይታ ሶዶ ጉብኝታቸው፤ አካባቢው አረንጓዴ ኢትዮጵያን የመገንባት ሀገራዊ ጽኑ ፍላጎት ምስክር መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አምርተው በክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ እና አከባቢ ያለውን የኮሪደር ሥራ እና የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴዎች ያስገኙትን ተጨባጭ ለውጥ ተመልክተዋል።
በተለይም ደግሞ ከአሶሳ የተወሰኑ መቶ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘውን የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ አስደናቂ የሥራ ውጤትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተመልክተዋል።
 
 
ማዕድን በብዝኃዘርፍ የልማት ምልከታችን አንዱ ቁልፍ ዘርፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቤኒሻንጉልጉምዝ ክልልም ለዚህ ርዕይ መሳካት ዐቢይ ሚና ያለው መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በአካል ተገኝተው ለመመልከት ባደረጉት ተከታታይ እንቅስቃሴ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የአለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል-ጎሮ-ቪአይፒ ኮሪደር ተመልክተዋል።
ሌላው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ወር ያከናወኑት ተግባር፣ በመደመር ሐሳብ ላይ የጻፉት አራተኛውንና "የመደመር መንግሥት" የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ያደረጉት ሰፊ ቃለ መጠይቅ ነው።
በዚህ ማብራሪያቸውም የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሐሳብ የወልና ገዥ እንዲሆን የሚያስቸሉትን በርካታ ሂደቶችን ያለፈ መሆኑን ገልጸዋል።
 
 
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ በተለይም ደግሞ የመደመር ፍልስፈናና እሳቤ የጠራ እና በሰፊው ተቀባይነት ያለው የአስተዳደር ሞዴል፣ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ትልምን የቀረፀ እና የህዝብ አመኔታ የተረፈ መሆኑን ገልጿል።
በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ግበርና ሽግግር ትልቅ እጥፋት እንደሆነ በታመነው የመንግሥት ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና የዳንጎቴ ግሩፕ በጎዴ አካባቢ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ ለማቋቋም ተፈራርመዋል።
የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ፕሮጀክት በአመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን በዓለም ከግዙፎቹ ፋብሪካዎች ተርታ የሚመደብ ይሆናል።
በአርባ ወራት እንዲጠናቀቅ እቅድ የወጣለት ፕሮጀክት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ኢትዮጵያን ከውጭ ከማስመጣት ጥገኝነት ነፃ በማውጣት የቀጠናው የማዳበሪያ ምርት ማዕከል ያደርጋታል።
በጥቅሉ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በሚመለከት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ምልከታ ያደረጉበት እና የፕሮጀክቶች እንቅስቀሴ እንዲፋጠን በአካል ተገኝተው አቅጣጫ ያስቀመጡበትም ጭምር ስኬታማ ወር ነው።