Search

ጊዜው የኢትዮጵያ ትንሳዔ ወቅት እንደመሆኑ የጀመርናቸውን ሥራዎች በስኬት ማጠናቀቅ እንዲቻል ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 35

ጊዜው የኢትዮጵያ ትንሳዔ ወቅት እንደመሆኑ የጀመርናቸውን ሥራዎች በስኬት ማጠናቀቅ እንዲቻል የአዲስ አበባን ትልቅነት የሚመጥን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የሰለጠኑ 5ኛ ኮርስ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ፤ ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ በበጎ ተግባር የተሰማሩ 275 ሺህ የሰላም ሠራዊት አባላት የከተማዋን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ሚናቸዉ የጎላ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ ማንሰራራት ግድ ማይላቸው ባንዳዋች እና ባዳዎች እኩይ ሴራቸው እድል ፈንታ እንዳያገኝ እና ሰላማችን እንዳይደፈርስ ዓይናችንን ሳንነቅል ነቅተን ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና በመውሰድ ወደ ሥራ የተሰማራው የሰላም ሠራዊቱ፣ የከተማዋን ነዋሪ በማሳተፍ በሰላምና በፀጥታ ጉዳይ የበኩሉን አስተዋጾ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በዛሬው ቀን በህዝባዊ የፀጥታ አደረጃጀት የታቀፉ 11 ሺህ የሰላም ሠራዊት አባላት ከንቲባ አዳነች አበቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል።
በምንተስኖት ይልማ