Search

የመውሊድ በዓልን ስናከብር የሀገርን ሰላም በማስጠበቅና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል፡-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 45

1500ኛውን የነቢዩ መሐመድ መውሊድ (ልደት) ስናከብር የሀገርን ሰላም በማስጠበቅና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ሐሙስ ነሐሴ 29/2017 የሚከበረውን የመውሊድ በዓል አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማም ሼህ ጠሃ መሐመድ ሃሩን በመግለጫው እንደገለፁት፤ ነቢዩ መሐመድ ለዓለም ሰላምና ለሰው ልጆች እዝነት የተላኩና የሰሩ በመሆናቸው ሙስሊሙ ማህበረሰቡ አርዓያነታቸውን ሊከተል ይገባል፡፡
በመውሊድ በዓል አከባበር ወቅት የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱና በዓሉ የእስልምና አስተምህሮን ለእምነቱ ተከታዮች ለማስረፅ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ አባልና የወጣቶችና ሴቶች ዘርፍ ተጠሪ ሼህ አብድልሃሚድ አህመድ በበኩላቸው፤ መውሊዱ ሲከበር የአካባቢን ሰላም በማስጠበቅና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደ ሚገባ ገልፀዋል፡፡
በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ እንደሚከበር የተገለፀ ሲሆን፣ በአዲስ አበባም በታላቁ አንዋር መስጊድ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ሃገራት ኤምባሲዎች አምባሳደሮችና ምእመናን በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ተጠቁሟል፡፡
በመሐመድ ራህመቶ