Search

የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሰራ ነው፡- ሙስጠፌ ሙሕመድ

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 45

ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሰራ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ ሙሕመድ ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በቶጎ ውጫሌ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና የትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት የቶጎ ውጫሌ ከተማ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የመጠጥ ውኃ፣ የጤና እና የትምህርት መሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ያነሱ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ በ2017 ዓ.ም የከተማዋን የመጠጥ ውኃ ችግር ሙሉ ለሙሉ የሚቀርፍ ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል።
በአጭር ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት የሚበቁ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስጀመራቸውን ገልጸው፤ ይህም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግስት ቅርጠኛ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሴ አህመድ በበኩላቸው፤ በተለይ የሆስፒታሉ መገንባት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጅግጅጋ የሚደረግ ጉዞን በማስቀረት የቀዶ ጥገና፣ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና፣ ለተኝቶ እና ለተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
መንግስት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ያሉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ሼክ አደን፤ በቶጎ ውጫሌ የተጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቤተ-መፅሐፍት፣ የአይ ሲ ቲ እና ቤተ ሙከራን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል።
ግንባታዎቹን በ18 ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እንደሚሰራም ተጠቁሟል።
በቴዎድሮስ ታደሰ