Search

በአፍጋኒስታን በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር ከ620 አልፏል

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 42

በአፍጋኒስታን ምስራቃዊ ክፍል በደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር ከ620 በላይ መድረሱን የሀገሪቱ የጊዜያዊ የታሊባን መንግሥት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
እሁድ ምሽት ላይ በኩናር እና ናንጋርሀር ግዛቶች ላይ ያተኮረው በርዕደ መሬት መለኪያ ሬክተር ስኬል 6 መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በበርካታ መንደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
የመንግሥት ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ የሟቾች ቁጥር ወደ 800 ከፍ ሊል እንደሚችል እና የቆሰሉትም ከ2 ሺህ 500 በላይ መሆናቸውን ገልጿል።
የአደጋው መጠን ትልቅ በመሆኑ እና መንገዶች በመዘጋታቸው የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሰዎችን ከህንጻ ፍርስራሽ ለማውጣት እና እርዳታ ለማቅረብ እየሰሩ ነው። ይሁን እንጂ የርቀት መንደሮች ተደራሽ አለመሆናቸው የእርዳታ ስራውን እያስተጓጎለ ነው።
የአፍጋኒስታን መንግሥት ዓለም አቀፍ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ሀገሪቱ በ2023 ከደረሰባት ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ እንደገና ያጋጠማት አደጋ ነው።
በሰለሞን ገዳ