Search

ከዓባይ ትርክት ቀያሪ ዜማዎች አንዱ - "ጭስ አልባው ነዳጄ"

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 43

ኪነ ጥበብ ስለ ዓባይ ብዙ ብላለች። በዓባይ ስለ ትካዜ፣ በዓባይ ስለቁጭት፣ በዓባይ ስለውበት፣ በዓባይ ስለአንድነት፥ ተገጥሟል፤ ተፅፏል፤ ተቀንቅኗል። ተተውኗል ብቻ በጥበብ ዓባይ ያልተዳሰሰበት፣ ያልታየበት መስክ የለም።

ዓባይ ግንድ ይዞ መዞሩ፣ የማያረጅ ውበቱ፣ ሕዝቡ የበይ ተመልካች መሆኑ በኋላም የዓባይ ታሪክ መቀየሩ ከተገለጠባቸው የጥበብ ዜማዎች መካከል ስለ አንዱ እናውሳችሁ።

ድምፃዊ ገነት ማስረሻ - “ጭስ አልባው ነዳጄስትል ያዜመችው ሙዚቃ የዓባይን የዘመናት ታሪክ ከሚያሳዩ ዜማዎች አንዱ ነው። ይህ ሙዚቃ የሚጀምረው በዚህ ስንኝ ነው

"ዓባይ ነጋ ጠባ ሀብቱን ያፈሰዋል፤

ጭስ አልባው ነዳጄ ብለው ምን ያንሰዋል"

ይህ በሁለት መስመር ስንኝ የተቋጠረ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት ነው። ኢትዮጵያን ሰንጥቆ ድንበር እስኪሻገር ዓባይ ግራ እና ቀኙ ላሉ ጎጆዎች ብርሃን ሳይሰጥ፤ ለወገኑ ሳይበጅ ሆድ እንደባሰው ተጓዥ ቁልቁል እየተንደረደረ የሀገር ሀብት ተሸክሞ ይነጉድ ነበር።

ይህ የዘመናት ታሪክ ተቀይሮ ዓባይም ጉባ ላይ አርፎ፤ ኤሌክትሪክ ያመነጫል፤ ኢትዮጵያም ለዘመናት ሲሰደድ ከቆየው ሀብቷ ትጠቀማለች ሲባል የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት እና የአንድነታቸውም ኃያልነት ታየ።

"ዘመን ቢያስታርቀን ከዓባይ ብንስማማ፣

ይዘን ተጠጋነው አካፋ እና ዶማ"

ይህ አልደፈር ብሎ የቆየውን ዓባይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ጠላጥትን መክተው ሀገር እንዳፀኑ ሁሉ፤ በራሳቸው አቅም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ እውን ለማድረግ የጀመሩትን ጉዞ የገለጠ የሙዚቃው ክፍል ነው።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዓባይ የዘመዱ ያህል ቅርቡ ነው። ዓባይ የታላቅነትም ማሳያ ነው። የመሰብሰብ፣ የአንድነት ምልክት ነው። ከሰከላ ተነሥቶ የሱዳንን ድንበር እስኪሻገር የዓባይ ወንዝን እያገዘፉ እና ኃያል እያደረጉት የሚመጡት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ ዓባይ የሚቀላቀሉ ገባሮቹም ናቸው። የዓባይ እና የኢትዮጵያውያን ቁርኝትም ቅርብነቱ በዚህ ልክ ነው።

"ዓባይ እኔ እና አንተ ያለነው ቅርብ ነው፣

ከተስማማንማ ሙያ በልብ ነው"

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዞ ላይ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ይልቁንም ዓለም ፊቱን አዙሮብን፣ ብድር ተከልክለን፣ ከሳሾቻችን በዝተው ፈተናዎችም ተደራርበው ነበር።

ኢትዮጵያ የዓባይን ጉዳይ በፍትሐዊነት በመጠቀም እንተባበር ብትልም ከሳሾቿ ግን እስከ የዓለም የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ አቁመዋታል።

ድርድር አፍርሰዋል፤ በቅኝ ግዛት ስምምነት ላይ ተገትረውእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልሲሉም ከርመዋል። በዚህ ሁሉ መሐል ግን ከዓባይ የተስማሙት ኢትዮጵያውያንሙያ በልብ ነውብለው በጉባ ሰማይ ሥር ቀን ከሌት በሀገራቸው ጎጆዎች ብርሃን ለመፈንጠቅ ሲተጉ ነበር።

"ስንት ዘመን ሐሳብ ስንት ዘመን ቁጭት፣

ስንት ዓመት በጣሳ ስንት ዓመት በወጪት"

ከሐሳብ የተሻገረ የልማት፣ የድል፣ የብርሀን እና የአንድነት፤ የኢትዮጵያውያን ማሕተም እነሆ ጉባ ላይ እውን ሆነ።

ዓባይ በወጪት ሳይሆን በግድብ ተደፈረ። እያለን እንደሌለን፤ ተሰጥቶን እንዳልተሰጠን፤ ዓይተን እንዳለየን ሰንተላለፍ ከቆየነው ዓባይ ጋር ጉባ ላይ ቃልኪዳን አሰርን።

ቁጭትንም እነሆ ታሪክ አደረግነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብንም በአንድነት እና በተባበረ ክንድ እውን አደረግነው። ገነትም በሙዚቃዋዓባይ ትርክትህን እንዲህ ቀይረነዋልትለዋለች፦

"ማደሪያ ሳይኖረው ግንድ ይዞ ይዞራል

የሚባለው ተረት ከእንግዲህ ይቀራል፤

እንዲህ እንደዛሬው መልካም ቀን ሲመጣ፤

ግንድም ይዘህ አትዞር ማደሪያም አታጣ!"

የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ሳይጎዳ ብሎም የውኃ ድርሻቸውን ሳይቀንስ፤ ከጎርፋ አደጋ እና ከድርቅ የሚጠበቅ የውኃ ፍሰትን የሚያረጋግጠው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ለቀጣናው ልማት እንጂ ስጋት አለመሆኑን ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱን ግልጽ አድርጋ ለባለሙያዎች በማሳየት አረጋግጣለች።

ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ተከታይ ናት፤ ገነትም በሙዚቃዋ ጎረቤቶችንአትስጉ ዓባይ ለሁላችንም በቂ ነውትላቸዋለች፦

"በፍቅር ብንይዘው ዓባይ የሀገር ዋርካ፣

ለዓለም ይበቃል እንኳን ለአፍሪካ"

በሰለሞን ከበደ