Search

የኢትዮጵያውያን አንድነት ማሰሪያ መቀነት!

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 52

ኢትዮጵያ በጋራ ሀገር የመገንባት ባህል ያላቸው ሕዝቦች እናት ናት፤ ይህ የአንድነት ባህላቸውም ከእያንዳንዱ ቀዬ እና መንደር ይጀምራል።

በጋራ አርሶ መዝራት፣ አጭዶ መሰብሰብ፣ ልጆችን መዳር፣ በኀዘን ጊዜ አብሮ ማዘን የአንድ አካባቢ ባህል ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን የኑሮ ዘይቤ ነው።

ሥነ-ልቦናችን መተጋገዝ፣ መተባበር እና በአንድነት የመኖር አስፈላጊነትን መረዳት ላይ የተገነባ ነው።

ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው በጠራቻቸው ጊዜ በየትኛውም ሁኔታ ሁሉ በጋራ መገኘትን ያውቁበታል።

ጠላት ሲመጣ “የእዛኛው አካባቢ ጉዳይ አያገበኛም” አይሉም፤ በአንድነት ወጥተው የሕይወት መሥዋዓትነት ጭምር ከፍለው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ያስከብራሉ፤ ይህንን በተደጋጋሚ አስመስክረዋል።

በተለይ በዓድዋ ጦርነት ያሳዩት አንድነት ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ የሚደነቅበትን አኩሪ ድል እንዲጎናፀፉ አስችሏቸዋል።

ይህንን አንድነታቸውን ታዲያ ከፍ ባለ ልማትም የሚያስመሰክሩበትን ጊዜ ሲጠባበቁ ኖረዋል።

ያ ጊዜ ደረሰና ከረጅም ዘመናት በፊት በሐሳብ ጥንስስ የነበረው አንድ ታላቅ ግድብን በዓባይ ወንዝ ላይ የመገንባት ሕልም ከዛሬ 14 ዓመት በፊት በተግባር ተጀመረ።

“ሚሊኒየም ግድብ” በሚል የተጀመረው እና በኋላም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚል የቀጠለው ግዙፉ ፕሮጀክት እውን ለመሆን የኢትዮጵያውያንን የተባበረ ክንድ ፈለገ።

ይኼኔ ታዲያ ሀገር ስትጠራው ቀድሞ መገኘትን ባህሉ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በኑሮ እና በእውቀት ደረጃ ሳይከፋፈል በአንድነት ለልማቱ ተመመ።

ከሰል ሽጠው የሚተዳደሩ እናቶች የአቅሜን ለሀገሬ አሉ፤ አዳጊዎች ዶሮ ሽጠው ቦንድ ገዙ፤ አርሶ አደሩ ለሀገሬ እኔም አለሁ ሲል አለኝታነቱን አረጋገጠ።

ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ሐሳብ ያለው በሐሳቡ፣ ተሰሚነት ያላቸው ተናግሮ በማሳመን ችሎታቸው ሁሉም ለዚህ ታላቅ ዓላማ ተረባረበ።

የብርታት፣ በፈቃድ አብሮ የመሥራት እና የአንድነት ታሪካችንም በዐይን በሚታይ ግዙፍ ውጤት ሊመዘንም ዕድል አገኘ።

የብድር እና የፋይናንስ ድጋፍ እጦትን ብሎም ዲፕሎማሲያዊ ጫናን በመቋቋም የተጀመረው ፕሮጀክቱ በየመሐሉ ባጋጠሙት እንቅፋቶች ምክንያት በተባለለት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ቆየ።

ከእነዚህ እንቅፋቶች መካከልም በዋናነት የሚጠቀሰው በቀድሞው ‘ሜቴክ’ የተከሰተው የአፈፃፀም ችግር ነበር።

ሜቴክ የግድቡን የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ ለመሥራት ጣልቃ ከገባ በኋላ በሚፈለገው ልክ መፈፀም አልቻለም፤ የግንባታ ሂደቱም ተስተጓጎለ።

በወቅቱ የሲቪል ሥራውን ሲሠራ የነበረው ሳሊኒ ኩባንያ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ቢወጣም ሜቴክ በአንፃሩ የኤሌክትሮ መካኒክ ሥራዎችን እያጓተተ የመላ ኢትዮጵያውያንን ሕልም እስከማደብዘዝ ደረሰ።

የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ ከጀመራቸው የሀገርን ብልጽግና እውን የማድረግ ሥራዎች አንዱ ይህንን እክል ማስተካከል ነበር።

አጠቃላይ የሕዳሴ ግድብ ሥራውን ሳሊኒ ኩባንያ እንዲጨርስ የማግባባት ሥራ በመሥራት እና ካሣ በመክፈል ጭምር ግድቡ እንዲፋጠን መንግሥት አቅጣጫ አስቀመጠ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያደረጉት ብርቱ ክትትልም ኢትዮጵያን በጉጉት የሚጠብቁት ግድብ እውን እንዲሆን ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ግድቡ በታሰበው ጊዜ ባይጠናቀቅም ይኸው አሁን ደርሶ “እንኳንም መሥዋዕትነት ከፈልንለት” የሚባል ውጤት አስገኝቷል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጋራ ማሳካት ከቻልናቸው የልማት ታሪኮች መካከልም ከእስካሁኖቹ ትልቁ ሊባል የሚችል ፕሮጀክት ሆኗል።

ይህ ፕሮጀክት በግንባታ ሂደቱ ላይ ከፋይናንስ ድጋፍ እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በርካታ ተግዳሮቶችን አልፏል።

ነገር ግን ጠንካራው የኢትዮጵያውያን አብሮነት እና አንድነት እያንዳንዱ እርምጃው ወደ ፊት ብቻ እንዲሆን አስችሎታል።

ለሀገራችን ኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲሁም ለቴክኖሎጂ እና ለሙያ ሽግግር ጉልህ አስታፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ ለዘላቂ ዕድገት መሠረት የሚሆን ፕሮጀክት ነው።

ይህ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው፤ ከአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ግቦች መካከል አንዱ አህጉሪቱን በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተሳሰር ነው።

የሕዳሴ ግድብም ይህንን ግብ ለማሳካት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አንዱ ታላቅ ፕሮጀክት እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ትሥሥር የሚያጠናክር ነው ልንለው እንችላለን።

ለሀገራችን የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ባሻገር የኢንዱስትሪ ዕድገትን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር እና የሕዝብን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ አስተዋፅኦው የጎላ ነው።

የኢትዮጵያውያን የጋራ ራዕይ እና ጠንካራ የመንግሥት አመራር ሰጪነት የወለደው የሕዳሴ ግድብ፣ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ያሰሩበት መቀነት ነው።

ሀገራችን የተሻለ የብልጽግና መንገድ ላይ መሆኗን የሚያሳይ እና ኢትዮጵያውያን የልጆቻቸውን ብሩህ መፃኢ ጊዜ የሠሩበት ታላቅ ፕሮጀክት ነው።

ይህንን ደማቅ ታሪክ መጻፍ የቻላችሁ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ!

በዮናስ በድሉ