ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ከሐይማኖታዊ መርህ ውጪ ጥላቻን የሚሰብኩ አካላት ከስህተታቸው ሊታረሙ ይገባል ሲሉ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት አካሂዷል።
ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት፤ ከሐይማኖታዊ መርህ ውጪ ጥላቻን የሚሰብኩ አካላት ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት የበጎነት ማሳያ እና የድሆች መጠገያ ሆነው የኖሩ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ነገር ግን አንዳንዶች ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ከኃይማኖታዊ መርህ ውጪ ከፍቅር ይልቅ መነጣጠል እና ጥላቻን ሲዘሩ ይስተዋላል ብለዋል።
በማኀበራዊ ሚዲያ ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ጥላቻ የሚሰብኩ አካላት ሊገሰፁ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በ17ኛው ጠቅላላ ጉባኤም ይህንኑ ድርጊት ትኩረት ሰጥቶ ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የኃይማኖት ተቋማት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሚናቸውን በመወጣት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መሰረት ሊጥሉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የኃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመስከረም ቸርነት
#EBC #ebcsotstream #Religion #Peace