Search

በዚህ ትውልድ መልስ ያገኘው የዘመን ቁጭት

ሰኞ ነሐሴ 26, 2017 100

በቅድመ አያቶቻችን የነበረው ቁጭት በዚህ ትውልድ መልስ አግኝቷል ሲል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ገለፀ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር ከኢትዮጵያ ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የዘመናት ቁጭት የሆነውን የህዳሴ ግድብ ከዳር በማድረስ ትውልዱ ትልቅ ታሪክ ሰርቷል ብለዋል፡፡

ትውልዱ የህዳሴ ግድብን ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን ባላው ሂደት በመተባበር እና በመደጋገፍ እዚህ እንዲደርስ አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን በጉልበት የሞራል እና የእውቀት ድጋፍ ይደረግ ነበር ያሉት ወ/ሮ ፍቅርተ፤ ላለፉት 14 ዓመታት ያለማቋረጥ ህብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት ያደረገው አስተዋጽኦ የሚደነቅ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመንግስት ሰራተኛው፣ አርሶ አደሩ፣ ፖሊስ እና መከላከያ እንዲሁም ሌላው የማህበረሰብ ክፍል በ8100 የሞባይል አጭር ጽሁፍ መልዕክት ብር በመላክ፤ እናቶች ካላቸው ጥቂት ገንዘብ በተደጋጋሚ ድጋፍ በማድረግ ተሳትፏቸውን አሳይተዋልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው ያደረገው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ ፍቅርተ፤ ህይወታቸው ካለፈ በኋላም ለህዳሴ ግድብ ሀብት ንብረታቸውን የተናዘዙ እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

የዲፕሎማሲ ጫናዎች በሚመጣም ጊዜ የህዝቡ ድጋፍ እንዳልተለየ እና ለዓለም አቀፉ የጸጥታው ምክር ቤትም ድምፃቸውን ማሰማታቸውንም ገልፀዋል፡፡

"ከዚህ ፕሮጀክት የተማርነው መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን የሚያደርገው የተቀናጀ ስራ በየትኛውም ችግር ውስጥ ቢያልፍ ለስኬት እንደሚደርስ ነው" ብለዋል፡፡

በሜሮን ንብረት

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD