Search

አሜሪካውያን ከድባቴ የወጡበት የሁቨር ግድብ እና የሃያልነት ትዕምርታቸው

ማክሰኞ ነሐሴ 27, 2017 3020

የአሜሪካው ሁቨር ግድብ የአሜሪካ ኢንጂነሪንግ ዕድገት እና የማድረግ አቅም ተምሳሌት ነው። ይህ ግድብ በአሪዞና እና በኔቫዳ ግዛቶች ወሰን አካባቢ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባ ግዙፍ የኮንክሪት ቅስት ግድብ ነው።

ግድቡ የሰው ልጅ በጥንካሬ እና በብልሃት ተፈጥሮን እንዴት በቁጥጥሩ ሥር ማዋል እንደሚችል ማረጋገጫ ምልክትም ተደርጎ ይወሰዳል።

በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ፣ የኮሎራዶ ወንዝ በደቡብ ካሊፎርኒያ ውስጥ የእርሻ ቦታዎችን በጎርፍ ጠራርጎ በመውሰድ የአካባቢ ነዋሪዎች የሀዘን ምንጭ የነበረ ነው። በአካባቢው የእርሻ ሥራ ለማከናወን የሚተጉ አሜሪካውያን የኮሎራዶ ወንዝ ጥፋት እንዳይመጣ በመፅለይ ጭምር ነው። ምክንያቱም ባንድ ቅጽበት ኮሎራዶ ሁሉን ነገር ጠራርጎ የነበረውን እንዳልነበር በማድረግም ይታወቃል።

በሌላ በኩል ደግሞ ደረቃማ የሆኑት የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ለመስኖ እና የሕዝቡን ብዛት ያማከለ አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት በጣም ያስፈልግ ነበር። በረሃውን ለብቻው እየጋለበ የሚጓዘው ኮሎራዶ ሲሳይ መሆን ሲችል መርገም የሆነባቸው አሜሪካውያን የወንዙን መረጋጋት አጥብቀው የሚሹት ተስፋቸው ነው።

በተቃራኒው ደግሞ እያደገ የነበረውን የአሜሪካን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከወንዙ ውኃ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት በጣም አስፈላጊ የሆነበት ወቅትም ነበር።

እናም አሜሪካውያን ጎርፉን መቆጣጠር፣ ለመስኖ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ውኃ ማከማቸት ብሎም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሟላት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጾ ሥራ መጀመር የወቅቱ መንግሥት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው

ወንዙን የሚያዋስኑ ሰባት ግዛቶች የውኃ አጠቃቀምን መብት ለመመደብ የኮሎራዶ ወንዝ ስምምነት በ1922 ከተፈረመ በኋላ የአሜሪካ ምክር ቤት በ1928 የ"ቦልደር ካንየን ፕሮጀክት ሕግ" አጽድቆ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ፈቀደ።

ይሁን እንጂ አሜሪካ በታሪኳ ጥቁር ጠባሳ ብላ ካሰፈረቻቸው መጥፎ ታሪኮች ውስጥ አንዱ የሆነው የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ነበርና እንዲህ ያለ ግዙፍ እና ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ፕሮጀክት መጀመር ቅብጠት ነው የሚሉ ቀላል አልነበሩም።

ስለሆነም ግንባታው የተጀመረው በ1931 አሜሪካ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት(Great Economic Depression) ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከመላ ሀገሪቱ ወደ አካባቢው ለሚጎርፉ በሺህ የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊ ሰዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድልን እንደሚፈጥር እና አሜሪካውያን ከገቡበት ድባቴ ለማውጣት ይጠቅማል ያሉ መሪዎች ጉዳዩን በችግር ውስጥም ቢሆን ሆነው ሥራውን ለማስጀመር ወደኋላ አላሉም።

"ስድስቱ ኩባንያዎች" በሚል ስያሜ የሚታወቁት የስድስት የግንባታ ድርጅቶች ኮንሶሪየም የግንባታውን ኮንትራት ወስዶ ሥራውን ሠርቷል። ኩባንያው ሠራተኞቹ እና ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩበትን "ቦልደር ሲቲ" የተባለ ጊዜያዊ ከተማም መሰረተ።

ሠራተኞች በመጀመሪያ አራት ግዙፍ ዋሻዎችን በመቆፈር ኃይለኛውን የኮሎራዶ ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ነበር ሥራቸውን የጀመሩት። ወንዙ የሚጓዝበት ቦታ ሸለቋማ በመሆኑ ዋሻ ሰርቶ የውሃን አቅጣጫ ማስቀየር ቀላል ሥራ አይደለም። ብዙዎች ህይወታቸውን ያጡለት እና ትልቅ የኢንጅነሪንግ ጥበብን የሚጠይቅ ነው።

የሙቀቱ መጠን ከ100 ዲግሪ ፋራናይት በላይ በመሆኑ ለአሜሪካውያን ሠራተኞች ይህ በጣም አስቸጋሪና አደገኛ ቢሆንም ለሀገራቸው ትንሣኤ ላባቸውን እና ደማቸውን ሰጥተው የታሰበውን እውን አድርገዋል

ግንባታው በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ሁቨር ግድብ ከተያዘለት የመጠናቀቂያ ጊዜ አስቀድሞ በ1936 ተጠናቀቀ። በግንባታው ወቅት በአደጋ እና ከሙቀት ጋር በተያያዙ በሽታዎች ሳቢያ ከ100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለግንባታው የዋለው የኮንክሪት መጠን ከሳን ፍራንሲስኮ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ የሚወስድ ባለ ሁለት መስመር አውራ መንገድም ማሠራት የሚችል ነበር።

በእርግጥ የሁቨር ግድብ የመስኖ ፕሮጀክት ወይም የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ  ብቻ አይደለም። በወቅቱ ከባድ ከነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ለመውጣት የብርሃን ቀዳዳ ያገኙበትም ነው። በወቅቱ ለግድቡ ሥራ ያስፈልግ የነበረው የሰው ሃይል ብዙ በመሆኑ ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ለግድቡ ሲባል የተገነባው መንገድ እና የተመሰረተው ከተማ ደግሞ ሌላ ያልታሰበ ሲሳይ ይዞላት የመጣው አሜሪካ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ሁቨር ዳም የተኛው ኢኮኖሚዋ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆኖላታል። 

ከተጠናቀቀ በኋላ "የቦልደር ግድብ" ተብሎ እንዲሰየም ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ሬይ ላይማን ዊልበር "የሁቨር ግድብ" የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ይህም 31ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኸርበርት ሁቨር በፕሮጀክቱ ልማት ላይ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ መታሰቢያ እንዲሆን ነበር።

ይሁን እንጂ በፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት አስተዳደር ወቅት ስሙ ወደ "ቦልደር ግድብ" እንዲመለስ የተወሰነ ቢሆንም፣ በ1947 ግን በኮንግረስ ውሣኔ ስሙ በቋሚነት ወደ "ሁቨር ግድብ" ተመልሷል።

የሁቨር ግድብ አሁን 94 ዓመት የሞላው ሲሆን፣ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ ለሚገኘው ሚሊየን ሕዝብ የጎርፍ መቆጣጠሪያ፣ እንዲሁም የውኃ እና የኃይል ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ለአሜሪካ የኢንዱስትሪ ልማት ጥንካሬ፣ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ልህቀት ማሳያ፣ እንዲሁም ላባቸውን እና ደማቸውን ላፈሰሱ ሠራተኞች ጽኑ የሀገር ፍቅር ማረጋገጫ ማኅተምም ነው።

ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ አሜሪካውያን በሁቨር ግድብ እየተጓዙ ሲጎበኙ በአያቶቻቸው ጥበብ እና የሀገር ፍቅር ትጋት እንዲሁም ጥበብ እየተደነቁ የሚመለሱት። ይህ ብቻ አይደለም አሜሪካውያን ሀገራቸው ልዕለ ሃያል እንደሆነች እንዲሰማቸው ካደርጉ ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ አንደኛው ግድብ ሁቨር በመሆኑ በሄዱበት ሁሉ ታላቅነታቸውን ለመመስከር አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉት። 

በዓለም ላይ ልዕለ ሃያል ሆና ለመቀጠሏ ብዙ ምክንያቶች የምትደረድረው እና በርካታ የዕድገቷ ምስጢሮች የሚተነተኑላት አሜሪካ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት እነሱ (Great Economic Depression) የሚሉት ችግር ውስጥ ሆነው የተስፈነጠሩበት ቆራጥ ውሳኔ ይህ ነው። የአሜሪካውያን የኩራት ምንጭ፣ የመስፈንጠሪያ ታሪክ፣ ከድብርት እና ተስፋ መቁረጥ የወጡበት የአያቶቻቸው ቆራጥ የታሪክ እጥፋት የዛሬ ልዕለ ሃያልነት መመስከሪያቸው ሆኗል። 

በለሚ ታደሰ