Search

“ልጄ እኔ ካሳለፍኩት የተሻለ ሕይወት እንደሚኖራት አምናለሁ”፡- ሻይ እና ቡና በመሸጥ ለሕዳሴ ግድብ የላባቸውን ጠብታ ያዋጡት እናት

ማክሰኞ ነሐሴ 27, 2017 186

ወርቅነሽ ሹክሪ ይባላሉ፤ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በአነስተኛ የሻይ ቡና ንግድ ይተዳደራሉ።

ከ13 ዓመታት በፊት መንግሥት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይፋ ባደረገበት ወቅት በታላቅ ተነሣሽነት ቦንድ ገዝተዋል።

ከራሳቸውም አልፈው እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ቦንድ እንዲገዙ ሲያደርጉ እንደነበር ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።

እናት ሀገራቸውን በጣም እንደሚወድዱ የሚናገሩት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ የአንድ ሴት ልጅ እናትም ናቸው።

ሴት ልጃቸውን እንደ አባትም እንደ እናትም ሆነው ያሳድጉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ ሁሉም ወጪ ተሸፍኖላት በመንግሥት ትምህርት ቤት እየተማረች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

“ሀገሬ ልጄን በነፃ እያስተማረችልኝ ነው፤ እኔም የበኩሌን ለሀገሬ ማበርከት አለብኝ’’ በሚል የሕዳሴ ግድብ ቦንድ ለራሳቸው እየገዙ፣ ሌሎችም እንዲገዙ በማስተባበር የተሰጣቸውን ተልእኮ ማሳካታቸውን በኩራት ይናገራሉ።

የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ዙር ሙሌት በስኬት የመጠናቀቁን ዜና የሰሙ ዕለትም አስፋልት ዳር ወጥተው ደስታቸውን በእልልታ መግለጻቸውን ያስታውሳሉ።

አሁን ደግሞ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምርቃት በመብቃቱ “ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው” ሲሉ ነግረውናል።

“ለሕዳሴው ግድብ የላቤን ጠብታ ማዋጣት በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል፤ ይህ ለልጄ ነው፤ ልጄ እኔ ካሳለፍኩት የተሻለ ሕይወት እንደሚኖራት አምናለሁ፤ የደስታዬ ምንጭም ይህ ነው” ሲሉ ተስፋ በተሞላበት ስሜት ይናገራሉ።

የሕዳሴው ግድብ ግንበታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባለው የገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት መሳተፉ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።

እርሳቸው ባሉበት ክፍለ ከተማ ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከደሃ እስከ ሃብታም ሁሉም በራሱ ተነሣሽነት ተሳትፎ ሲያደርግ መመልከታቸውን ነው የነገሩን።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁ ለኢትዮጵያ እናቶች ትልቅ ብሥራት ነው ይላሉ - ወይዘሮ ወርቅነሽ።

“ግድቡ እናቶችን ከጭስ እና ከጭለማ ነፃ ሊያወጣቸው ደርሶላቸዋል” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል።

በቀጣይም በመንግሥት ለሚሠሩ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ልክ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ወይዘሮ ወርቅነሽ ሹክሪ ገልጸዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ

#EBC #ebcdotstream #GERD #resilience #hope #eraofnenewal