የ2017 ዓ.ም አምስቱ የጳጉሜ ቀናት ስያሜዎችን እና የአከባበር ሁኔታ አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፤ የጳጉሜ ቀናት መታሰብ ዜጎች ለአዲስ ዓመት የግላቸውን መሻት እውን ለማድረግ ሲያቅዱ የመንግስት መነሳሳቶች፣ እቅድ እና አቅጣጫዎችን በእቅዳቸው ውስጥ እንዲያካትቱ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተጠናቀቀው የ2017 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ፣ የኮሪደር ልማት፣ የኢንደስትሪዎች አምራችንትን ማጠናከር፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎችም ታላላቅ ሥራዎች የተከናወኑበት መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
በመጪው አዲስ ዓመትም እነዚህን እመርታዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ዋዜማ የሆኑትን የጳጉሜ አምስት ቀናትን በተለያዩ ስያሜዎች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን አመላክተዋል፡፡
ጳጉሜ 1 "የፅናት ቀን" ተብሎ መሰየሙን ገልፀው "ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር አመላክተዋል፡፡
"የኅብር ቀን" የሚል ስያሜ የተሰጠው ጳጉሜ 2 “ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያፀና እና የወል ትርክትን ብልጫ በሚያስይዝ መልኩ ይታሰባል፡፡
ጳጉሜ 3 "የእምርታ ቀን" ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መስኮች ሲመዘገቡ የነበሩ ስኬቶች እውቅና የሚያገኙበት ለቀጣይ ስኬቶች መበረታታት እና መነሳሳት የሚፈጠርበት ቀን መሆኑን ገልጸው፤ "እምርታ ለዘላቂ ከፍታ" በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ "ይህ ዓመት የማንሰራራት ዓመት ይሆናል" ባሉት መሰረት ጉልህ ስኬቶች የተመዘገቡበት ብቻ ሳይሆን የማንሰራራት ጅማሮ የታየበት ሆኗል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ጳጉሜ 4 "የማንሰራራት ቀን" በሚል ስያሜ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
ቀኑ "ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።
ጳጉሜ 5 "የነገው ቀን" በሚል ስያሜ የሚከበር ሲሆን "ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ" የሚል መሪ መልዕክት ተሰጥቶታል።
ነገን ከዲጂታል ዓለም ውጪ ማሰብ ስለማይቻል መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው 5 ጉዳዮች አንዱ 'ዲጅታላይዜሽን' መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቀናቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚከበሩ ጠቁመዋል።