በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት የተፈጠረው ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቅ “ንጋት” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ለሐይቁ የተሰጠው ስያሜ የኢትዮጵያውያን የወል ሃሳብ እንዲሆን የተፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩም፥ “በህዳሴ ግድብ ሥራ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደየአቅማቸው እና የሞያ ዘርፋቸው የተሳተፉበት በመሆኑ ነው” ብለዋል።
“ሕዳሴ የብዙዎች የሀሳብ፣ የሃብት፣ የጉልበት፣ የላብ እና የደም ድምር ውጤት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካቶች የሞቱለት፣ የቆሰሉለት፣ ያዋጡለት፣ የተከራከሩለትና የተጨቃጨቁለት ፕሮጀክት” መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያውያን የሆነን ፕሮጀክት ከአንድ ነገር ጋር ብቻ ማያያዝ ተገቢ አለመሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ መነሻ በግድቡ ምክንያት የተፈጠረው ሐይቅ ስያሜ የወል እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
ሰው ሰራሽ ሐይቁ “ንጋት” ሲባል ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ እንደነበረች እና ዓባይ ይህን ያህል ሃብት፣ ወርቅ እና አፈር ይዞ መሄዱን መገንዘብ አለመቻሏን የሚያስታውስ ነው።
ከዚህ ጥልቅ እንቅልፍ የነቃችው ኢትዮጵያ ብሩህ ቀኗን ገና እየጀመረች እንደሆነ ለማመላከት ሐይቁ በጠዋቱ የፀሐይ ወገግታ “ንጋት” ተመስሎ እንደተሰየመ ገልፀዋል።
ይህም ረጅሙ የጭለማ ጊዜ አብቅቶ የብርሃን ፍንጣቂ መታየት ሲጀምር ያለውን ጊዜ የሚያመላክት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ነጋላት፣ ጭለማው አበቃ፣ አሁን ምሽቱ ነጋ የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
“በዚህ ጊዜ ሰው ከጠለቀ እንቅልፍ ነቅቶ የሚንጠራራበት፣ ዓይኑን የሚያብስበት፣ ረጅም ጉዞ ለመጓዝ፣ የቀን ውሎውን ለመፈፀም የሚታጠቅት ሰዓት እንደመሆኑ፤ ኢትዮጵያም እንዲሁ ንጋቷ እንደመጣላት ግን ከፊቷ የተዘረጋ መስክ እንዳላት ማሳያ ነው” ብለዋል።
ንጋት ያለፍንበት የጠለቀ እንቅልፍ አብቅቶ ከፊታችን ያለውን መልካም ሥራ የምንጀምርበት የብርሃን ወቅት መምጣቱን ስለሚነግረን፤ ይህ ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቅ “ንጋት” በሚል መሰየሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብስረዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ
#GERD #nigat #ንጋት #Ethiopia