ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የኩስመና ታሪክ ማብቂያ" በሚል ርዕስ ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ፤ የተጉ እናቶች ልጆቻቸውን ለውጤት እንዳበቁ የተጉ ሠራተኞች ደሞ ሕዳሴን ለፍጻሜ አብቅተውታል ብለዋል።
የስራ ክትትል እና በጥዋት መነሳት የስኬት ቁልፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሕመም ሆነ በድካም ሳይበገሩ በማለዳ ነቅተው ወገባቸውን አስረው ቤታቸውን የሚያቀኑትን እናቶች እንደማሳያ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንድን ነገር ለመጨረስ ገና ሳይጀመር ጨርሶ የማየት አቅም እና ሌሎችም እንዲያዩት በከፍተኛ ዲስፕሊን የመስራት ሞራል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
መድኃኒት የሚወስድ ሰው አንድ እና ሁለት ቀን እየዘለለ ቢውጥ በሽታው እንደሚባባስ ሁሉ፣ ሥራ የመጨረስን ጣዕም ማየት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወጥነት እንደሚያስፈልገው ነው የሚገልጹት።
በትንሹ ያልታመነ ለትልቁ ስለማይታመን ማንም ድጋፍ አያደርግለትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሚሰራ ሰው ግን ሁሌም ይታገዛል ብለዋል።
በሴራን ታደሰ