የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኮንክሪት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ደምና የሕይወት መስዋዕትነት መገንባቱን የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ዕለት ጀምሮ ግድቡ እንዳይገባ ጫና ቢደረግም ከለውጡ በኋላ ግድቡ በአዲስ መልክ መገንባት ሲጀመር ጫናው በርትቶ መቀጠሉን አስታውሰዋል።
በግድቡ በ200 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ታሪካዊ ጠላቶች በሚመሩት የተልዕኮው ጦርነት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ቦምብ በመቅበር ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች እንዳይቀርቡ ከፍተኛ ጫና ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል።
ለግድቡ ግንባታ ግብዓት የሚያቀርብ ፋብሪካን ጭምር ለማውደም ሙከራ መደረጉን ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።
ኮንትራክተሮች ሥራ እንዲያቆሙና ከግንባታ እንዲወጡ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሲደረግባቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በግድቡ የግንባታ ሂደት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመከላከያ ሥራዊት አባላት የላብ፣ የደምና የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን ያስታወሱት ኢንጂነር ክፍሌ የመንግሥት ቆራጥ አመራር እና የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት የግድቡ ግንባታ በድል እንዲጠናቀቅ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
በሰብስቤ ኃይሉ