የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ነባር ስደተኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የቤተሰብ አባላቸውን ወደ ሀገሪቱ እንዲያስገቡ የሚያስችላቸውን አሰራር በጊዜያዊነት ማገዱን አስታውቋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቬት ኩፐር ለፓርላማ "አሰራሩ ከብዙ ዓመታት በፊት የተቀረጸው በጦርነት፣ በግጭት እና በስደት የተራራቁ ቤተሰቦችን መልሶ ለማገናኘት እና ለመርዳት ሲሆን፣ አሁን ግን የሚተገበርበት መንገድ ተቀይሯል" ብለዋል።
በመሆኑም የሀገሪቱ መንግሥት አዲስ የሚቀርቡለትን ማመልከቻዎች ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በጊዜያዊነት መቀበል ማቆሙን ነው የገለጹት፡፡
እንደ ዴንማርክ እና ስዊዘርላንድ ባሉ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሀገራቱ ለማስገባት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት እንደሚጠብቁ ኢቬት ኩፐር ገልጸዋል፡፡
በአንጻሩ በዩናይትድ ኪንግደም እንደዚህ አይነት ማመልከቻዎች ብዙውን ጊዜ ስደተኞች የመጠለያ ጣቢያዎችን ከመልቀቃቸው በፊት በአማካኝ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚቀርቡ ነው ያነሱት፡፡
ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እአአ ከ2019 ወዲህ የስደተኞች ማመልከቻ ቶሉ ማላሽ ባለማግኘቱ በሀገሪቱ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ያገኘ አንድ ስደተኛ ቤተሰቡን ለመውሰድ በዓመት ቢያንስ 29 ሺህ ፓውንድ ገቢ ማግኘት እና ተስማሚ መጠለያ ማቅረብ የሚኖርበት ሲሆን፣ ወደ ሀገሪቱ የሚገባው የቤተሰቡ አባልም መሰረታዊ የእንግሊዝኛ ክህሎት ሊኖረው ይገባል ተብሏል።
በጉዳዩ ላይ ተገቢ የሆኑ ሕጎች እስኪዘጋጁ እገዳው እንደሚቀጥል የሀገሪቱ መንግሥት መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሴራን ታደሰ