Search

ለቁማር ከፍተኛ ገንዘብ የሚመድበው ዓለም ለእንደነዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ፈቃደኛ አይደለም፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ማክሰኞ ነሐሴ 27, 2017 214

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የኩስመና ታሪክ ማብቂያ" በሚል ርዕስ ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ፤ ለቁማር ከፍተኛ ገንዘብ የሚመድበው ዓለም ለእንደነዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ፈቃደኛ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ስለ ዓባይ ልማት ሲነሳ በርካቶች ለምን እንደሚቆጡ እና እንደጥፋተኛ እንደሚመለከቱን ጥያቄ እንደሚሆንባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ይህ ሳይበግረን ግድቡን በራስ አቅም ገንብተን ማጠናቀቅ ችለናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ሕዳሴ ፍትሕን የሚፈልገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢ-ፍትሐዊው ዓለም ፍትሕን ጠብቆ የተቀጣበት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"እኛ ከብዙዎች ጋር ተባብረን አብረን ብንሠራ በወደድን ነበር" የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን ይህን ካልተዋችሁ የሚለው ቅድመ ሁኔታ እና እኛን እንደጥፋተኛ የሚያዩበት መንገድ ፈታኝ ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ስትገነባ ውኃው ሳይጎድል እየፈሰሰም በርካቶች ተቆጥተው ጉዳዩን እስከ ተመድ ፀጥታው ምክር ቤት የወሰዱበት መንገድ እጅግ አሳዛኝ እንደነበረም ነው ያነሱት፡፡
"የዓለም ተቋማት ለካዚኖ እና ለሆቴሎች ከፍተኛ ብድሮችን ሲሰጥ ይታያሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰውን ልጅ ለሚቀይሩ እንደ ሕዳሴ ግድብ ላሉ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ተናግረዋል፡፡
ፈጣሪ ዓለምን ሲፈጥር ለሁሉም እንዲበቃ አርርጎ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት ግን ዓለምን ወደ ስግብግብነት እንደቀየረው ገልጸዋል፡፡
ግድቡ ከተጀመረ በኋላ ደለሉ ሲቀር ወርቅ ጭምር እንደተገኘበት ጠቁመው፣ የበርካቶች ቁጣ ምክንያት የዚሁ ሀብታችን በሀገራችን መቅረቱ እንደሆነ መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፈራችንን እና ወርቃችንን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን በጨለማ ለተዋጡት በርካቶች በርሃን የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል፡፡
ዓለም በጉዳዩ ላይ የነበረው ዕይታ የተዛባ እንደነበር እና ይህን እውነታ ለዓለም ለመግለጥ ከፍተኛ ድካም የጠየቀ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በለሚ ታደሰ