በዓለማችን ከፍተኛ መጠን ያለውን ዓሳ በማምረት ቻይናን የሚወዳደራት የለም።
ቻይና የዓለማችንን 60 በመቶ የዓሳ ምርት የምታመርተው ከባሕር ወይም ከውቅያኖስ የውኃ አካላት ሳይሆን፤ እንደ ንጋት ሐይቅ በመሳሰሉ በሰው ሰራሽ መንገድ ከተሰሩ ሐይቆች፣ ወንዞች እና የውኃ ገንዳዎች ነው።
ቻይና በእነዚህ ሰው ሰራሽ የውኃ አካላት ተጠቅማ በምታመርተው የዓሳ ምርትም ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ የሚሆነውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ከመሸፈኗም በላይ ለዓለም ገበያም ታቀርባለች።
ቻይና በሰው ሰራሽ የውኃ አካላት ላይ ከሚመረተው የዓሣ ምርት የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም ከሩዝ፣ ስንዴ እና ከቆሎ ምርቶች ከምታገኘው ይበልጣል።
ቻይና ለብዙ ዓመታት እንደባህል የሰራችበትን በሰው ሰራሽ የውኃ አካላት ተጠቅሞ ዓሳን የማምረት ዘዴ አሁን ላይ በዘመናዊው መልኩ አሻሽላ ትልቅ ውጤት እያስመዘገበችበት መሆኑን የዓለም ምግብ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
የቆየውን የዓሳ እርባታ ዘዴ በዘመናዊ መልኩ ለመቀየርም ትላልቅ የዓሳ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ገንብታለች።
እነዚህ ግዙፍ የዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆኑ አሳዎችን አዘጋጅተው ለምግብነት ከማቅረባቸውም በላይ ተረፈ ምርቱን ለኃይል አቅርቦት ግብዓትነት የማዋል እንቅስቃሴ ጀምረው ስኬትም አግኝተውበታል።
እነዚህ ግዙፍ የዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደ የዓሳ ቆዳ፣ አጥንት እና የተለያዩ የዓሳ ተረፈ ምርቶችን ወደ ባዮጋዝ በመቀየር ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ከመፍጠራቸውም በላይ የአካባቢ ብክለትንም እየቀነሱ ይገኛል።
ቻይናም ሰው ሰራሽ የውኃ አካላትን ተጠቅማ ለዓለም ገበያ በምታቀርበው የዓሳ ምርት በዓመት እስከ 20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች።
በተመሳሳይ፣ ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረችው ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለዓሣ ምርት ማደግ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን በመጥቀስ የቻይናን ተሞክሮ በመቅሰም ዘርፋን ማሳደግ እንደሚቻል እየተገለጸ ነው።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አማካኝነት በተፈጠረው ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ በሚረዝመው ሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ የዓሳ እርባታ ተጀምሮ አመርቂ ውጤትም ታይቷል።
አዲስ በተፈጠረው ግዙፉ ንጋት ሐይቅን በዘመናዊ ሁኔታ መጠቀም ከተቻለ እምቅ አቅሙን ይበልጥ ወደኢኮኖሚ አቅም መቀየር ይቻላል።
በዚህም የንጋት ሐይቅን የዓሳ ሃብት በዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች በትክክል ጥቅም ላይ መዋል ከተቻለ ለሀገርውስጥ ፍጆታ የሚውለውን የዓሣ መጠን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር፣ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #China #fish