Search

"ለምርቃቱ ቀን ለቁጭቴ ማካካሻ የሚሆን ሙዚቃ አዘጋጅቻለሁ" - ድምፃዊት ገነት ማስረሻ

ማክሰኞ ነሐሴ 27, 2017 146

 
የዘመናት ቁጭት ሻሪው የዓባይ ውሃ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መተሳሰሪያ የሚሆንበት ብስራት ነጋሪ ድምፅ ከመሰማቱ ሶስት ዓመት አስቀድሞ አንድ ትንቢተኛ የተባለለት የሙዚቃ ለአድማጭ መድረስ ቻለ፡፡
 
ሙዚቃውም ጭስ አልባው ነዳጅ አሊያም ዓባይ የሚል መጠሪያን ይዞ ለሙዚቃ ወዳጅ ሲደርስ የሙዚቃ ግጥም ደራሲውን ተስፋ ብርሃንን በግጥም ድርሰት፤ ከበርካታ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ስራዎች ጀርባ አሻራውን ማኖር የቻለው ሙሉጌታ አባተን በዜማ ድርሰት እና በቅንብር ያሳተፈ ነበር፡፡
 
ከዚሀ የሙዚቃ ስራ ጋር በተገናኘ "ትንቢተኛዋ" የሚል ተቀፅላን ያተረፈችው የባህል ሙዚቃ አቀንቃኟ ገነት ማስረሻን በድምፃዊነት አሳትፎ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም በኋላ ዜማው ለሕዝብ መድረስ ቻለ፡፡
 
ይህ የሙዚቃ ስራ ለሕዝብ ከደረሰ ከ3 ዓመታት በኋላ ደግሞ በዓባይ ወንዝ ሳቢያ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ቁጭት የሻረ አንድ ብስራት ተሰማ፤ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሕዳሴ ግድብ መሰረተ ተጣለ፡፡
 
ይሄውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ብስራት ከዳር እስከ ዳር መላው ኢትዮጵያውያንን በደስታ ማዕበል ሲሞላ 'ትንቢተኛዋ' ለተባለችው አንጋፋዋ ድምፃዊት ገነት ማስረሻ ግን ደስታው እጥፍ ድርብ ነበር፡፡
 
"ጭስ አልባው ነዳጅ ስሙን ቀይሮ፤ ግጥሙን ቀይሮ መጣ እንጂ አባይን ያልወቀስኩበት ሙዚቃ የለም፡፡" የምትለው ገነት ማስረሻ "ከልጅነቴ ጀምሮ በወላጅ አባቴ አማካይነት ስለ ዓባይ ብዙ ነገር እየሰማሁ መምጣቴ ከፍ ያለው ቁጭት በእዚህ ሙዚቃ ውስጥ ተነስቶበታል፡፡" በማለት ትገልፃለች፡፡
 
ቁጭት ሻሪው ብስራት ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም እውን ሆኖ ከፍፃሜ የመድረሱ ነገር ሩቅ መስሎ ቢታይም ዛሬ ላይ ቀርቦ ግንባታው የመቋጫውን ምዕራፍ ተሻግሮ የመመረቂያው ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡
 
ሙዚቃው ትንቢተኛዋ የሚል ስያሜን እንድታገኝ ያደረጋት ገነት ማስረሻ ከግድቡን ምርቃት ዋዜማው ላይ የተገኘችበትን ጨምሮ ለሰባት ጊዜያት ጉባ ላይ ተገኝታ ግድቡን መመልከቷን ገልጻለች።
 
ግድቡ የምርቃቱ ቀኑ በተቃረበበተ በስፍራው ተገኝታ ያየችው ነገር የተለየ ስሜት እንደፈጠረባት አንስታለች።
 
"ያየሁት ግድብ በሰው ልጆች ክንድ እና ጭንቅላት የተሰራ እሰከማይመስለኝ ድረስ የሀገሬን ልጆች ሁሉንም አመስግኛለሁ" ስትል ድምፃዊት ገነት ማስረሻ ትናገራለች።
 
"የተመለከትኩት ነገር በደስታ ብዛት እራሴን መቆጣጠር እንዳልችል አድርጎኛል፡፡" ስትል ስሜቷን አጋርታለች፡፡
 
"ያየሁት ታሪክ በሰው ልጆች ክንድ እና ጭንቅላት የተሰራ እስከማይመስለኝ ድረስ የሀገሬን ልጆች ሁሉንም አመስግኛለሁ፡፡" ስትል የገለጸች ሲሆን "አሁን ላይ ደግሞ ሲመረቅ ለሀገር ልጆች የሚሆን ሙዚቃ አዘጋጅለሁ፡፡" በማለት ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ተናግራለች፡፡
 
 
 
በናትናኤል ሃብታው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: