ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ሕልም መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በሕብረት እውን ያደረጉት የሕብረታቸው የቃልኪዳን ምልክትም ነው፡፡ አባቶች ለልጆቻቸው አያቶች ለልጅ ልጆቻቸው የሚያወርሱት የዘመኑ ትውልድ የላብ እና የደም አሻራ ያረፈበት የመነሳት ምልክት ነው፡፡
ኢትዮጵያ “የአፍሪካ ውኃ ማማ” ብትባልም ለዘመናት በተደረገባት ጫና ውኃዋን ሳትጠቀም የኖረችበትን ቁጭት የተወጣችበት የማንሰራራት ጉዞ ማስፈንጠሪያም ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጉባ ላይ የዚህ ቁጭት መውጫ ብሥራት ከመሰማቱ በፊት በተለይ ግብፅ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት መብት እንዳይኖራት ብዙ ዓመታት ለፍተዋል መዓት ተንኮሎችም ቆፍረዋል። አንዴ በእንግሊዞች ታግዘው ኢትዮጵያን ለመውረር ሲሞክሩ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ሰላም የምታጣበትን መንገድ ሲቀይሱ እና ሰላም ሲነሷት ኖረዋል፡፡
በአውሮፓውያኑ 1929 እና በ1959 ደግሞ በእንግሊዝ አጋፋሪነት ሱዳንን አጃቢ አድርገው ‘የውኃ ክፍፍል’ የሚል የቅኝ ግዛት ውል ተፈራርመዋል፡፡ በዚህ ወቅት 85 በመቶ የዓባይን ውሃ የምትሰጠው ኢትዮጵያ አለመካተቷ ታሪካዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን የስግብግብነት ማሳያ ሆኗል። ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ በኩል ግብፅ ውኃ እንዳትጠማ በተደጋጋሚ ቃል ብትገባም እሷን ባይተዋር ያደረገውን እና ለሱዳን ጠብታ የሰጠውን ‘የውኃ ክፍፍል’ ስትቃወም ኖራለች፡፡
የ“ዓባይ ስጦታ ነኝ” የምትለው ግብፅ ግን ስምምነቱ ሳይበቃት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማንኛውንም ውኃ የተመለከተ ፋይናንስ እንዳታገኝ መሰናክል ስትፈጥር ኖራለች፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ ባልፈረመችው ስምምነት ላይ ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝ ላይ ፕሮጀክት ለመሥራት አስባ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ከጠየቀች "የውኃ ክፍፍል ስምምነት" እንድታመጣ የሚል አደናገሪ አንቀጽ በማስገባት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳታገኝ አድርገዋል፡፡
ግብፅ ተፅዕኖውን ያጠናከረችው በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ብቻ ሳይሆን በሀገራት ላይም የተናጠል ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማሳረፍ ጭምር ነበር፡፡
የግድቡ መሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ በእውነት ትሠረዋለች ብለው ያላመኑት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ወንዙን አቅጣጫውን ሲያስቀይሩ ድንጋጤ ውስጥ ገቡ፡፡ ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎችን በማስታጠቅ ኢትዮጵያን ሰላም ማሳጣት እና ለግድቡ የሚሄዱ ግብዓቶችን ከማሰናከል ጀምሮ ጉዳዩን እስከ ተመድ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰድ ያልገቡበት ቦታ አልነበረም፡፡
ይሁን እንጂ ለዘመናት በቁጭት ስለ ዓባይ ሲያንጎራጉሩ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የቁጭት እንጉርጉሮውን አቁመው ዓባይን ለማሳደር በመወሰናቸው መሰናክሎቹን ሁሉ በጽናት አልፈው የዓባይን የምሥራች ፍሬ ለመብላት ደረሱ፡፡ ኢትዮጵያውያን እናቶች ከመቀነታቸው፣ ልጆቻቸው ለዓባይ ጥብቅና በመቆም እና የግብፅን ፕሮፓጋንዳ በአደባባይ በመሞገት፣ በቦታው ተገኝተው ግንባታው ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሀሩሩን ችለው 24 ሰዓታት በመትጋት የኢትዮጵያን ሕልም እውን አድርገዋል፡፡
የፀጥታ አካላት እና የግድቡን ግብዓት የሚያጓጉዙ ባለሙያዎች በባዳ ተገዝተው አድፍጠው መንገድ ላይ በሚጠብቁአቸው ባንዳዎች የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡ “የፈሪ ዛቻ ቆይ ብቻ ቆይ ብቻ” እንዲሉ ግብፅ ጌቶቿን ተማምናም ብዙ ብትፎክርም በሰው ደጅ ያልደረሰችው ኢትዮጵያ በልጆቿ ጽናት ዓባይን ጉባ ላይ አስራው ከባይተዋርነት አትርፈዋለች፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ያለፈ ታላቅ ትርጉም ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡ ሕዳሴ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራቸውን ያኖሩበት የደም እና ላብ ማኅተማቸው ነው! ዓለም ፊቷን ብታዞርም ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ተአምር መሥራት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት ነው!
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን አብሳሪ ሆኖ ሊመረቅ ተዘጋጅቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ባበሰሩበት ወቅት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ኃይለማርያም ደሳለኝ ለግድቡ እውን መሆን ላደረጉት የአመራር ሚና ያመሰገኑትም ይህን የትውልድ ቅብብሎሽ ለማሳየት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ የኢትዮጵያ ማንሠራራት አብሳሪ መሆኑን የገለጹትም፣ “የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ፤ የደም ጠብታ፣ የላብ ጠብታ፣ የዕንባ ጠብታ፣ የውኃ ጠብታ ድምር ውጤት መሆኑን፣ ይህ ግድብ ሕያው ምልክት ሆኖ ለትውልድ ሲመሰክር ይኖራል” በማለት ነው።
በለሚ ታደሰ