በቢሊዮኖች ይታያል ተብሎ የሚጠበቀው ታላቅ ክስተት ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም እሁድ ምሽት ላይ ይከሰታል፤ በዚህም ጨረቃ ደም መስላ ትታያለች ሲሉ የሥነ ፈለክ ተመራማሪው ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀው የጨረቃ ግርዶሹ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት፣ በእስያ እና በአውስትራሊያ እንደሚታይም ነው በተለይ ለኢቢሲ ዶት ስትሪም የተናገሩት።
የጨረቃ ግርዶሹ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከአመሻሽ ከ12 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ጀምሮ እስከ 3 ሰዓት ከ52 ደቂቃ ድረስ እንደሚታይ ጠቁመዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ክስተቱን መመልከት የሚችሉ ሲሆን፤ ጨረቃ ደም መስላ ትታያለች ክስተቱም ደብዛዛ፣ በከፊል እንዲሁም ሙሉ ሆኖ በሦስት ክፍል ይታያል ብለዋል።
ክስተቱን ለመመልከት ምንም መሳሪያ የማያስፈልግና በዐይን ብቻ የሚታይ ሲሆን ይህም በዐይን ላይ ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ነው የገለጹት።
የጨረቃ ግርዶሽን ትርጉምን የሥነ ፈለክ ተመራማሪው ሲያስረዱም፤ ፀሐይ በስተ ምዕራብ አድማስ ጨረቃ ደግሞ በስተ ምስራቅ አድማስ በመሆን መሬት መካከላቸው ስትገኝ ጨረቃን እንዳናይ የሚያደርግ ክስተት ነው ብለዋል።
በሄለን ተስፋዬ