Search

ዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የገባውን ቃል አላከበረም - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

ረቡዕ ነሐሴ 28, 2017 72

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በፓሪስ የተገባው ቃል ባለመከበሩ ዓለም ዛሬ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቋን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ታየ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 2ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት መክፍቻ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ዓለማችን በአሁኑ ወቅት በአስፈሪ ሁኔታ በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች ትገኛለች፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ሕይወትን እያመሰቃቀለ ይገኛል ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን እያፈረሰ በርካቶችን ለረሃብ እና ለስደት እየዳረገ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

ከፓሪስ የአየር ለውጥ ስምምነት 10 ዓመታት በኋላም ዓለም አሁንም ወደ መሥመሯ አልተመለሰችም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ፍትሐዊነትን ለማስፈን የተገባው የፓሪስ ስምምነት ተዘንግቶ ዓለም ዛሬም በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነች ብለዋል፡፡

አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የምታደርገው አስተዋጽኦ እጅግ በጣም ትንሽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ችግሩን በትልቁ እየተጋፈጠች ያለችው ደግሞ ይህችው አህጉር እንደሆነችም ገልጸዋል፡፡

ይህን እውነታ ለመቀየር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው እንቅስቃሴ ዕድገትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫን እና የኃይል አቅርቦትን ያረጋገጠ መሆን እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካም የተገባላት ቃል ተግባራዊ ተደርጎላት ሀብቷን አሟጣ ለዕድገቷ፣ ከአረንጓዴ ልማቷ እና ለታዳሽ ኃይል አቅርቦት መጠቀም መቻል እንዳለባትም ጠቅሰዋል፡፡

አፍሪካ ባልሠራችው ጥፋት አማራጭ ውስጥ መግባት ሳይሆን፣ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላት ወደ አረንጓዴ ልማት ፊቷን ማዞር እንዳለባትም ነው ፕሬዚዳንት ታየ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ችግሩን ለመቋቋም ታዳሽ ኃይል እና አረንጓዴ ልማት ላይ አተኩራ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ፤ ለአፍሪካም ለዓለምም አርአያ ልትሆን እንደምትችል ፕሬዚዳንት ታየ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተገበረችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሯ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የአፈር መሸርሸርን እየተከላከለች የምግብ ዋስትናዋን እያረጋገጠች ትገኛለች፤ የደን ሽፋኗን አሻሽላ የውኃ ሀብቷን እየጠበቀች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ታዳሽ የኃይል ምንጭን ለማግኘት እየሠራችው ባለው ሥራ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሠርታ ማጠናቀቋን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ባለው የኮሪደር ልማት ከተሞቿን አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ እያደረገችው ያለውም ይህንኑ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ይህ በአመራር ቁርጠኝነት የመጣውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ሌሎች መንግሥታትም ተግባራዊ ማድረግ እና በውስጥ አቅም የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል መቀላቀል እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ከዓለም ፍትሕን ትፈልጋለች ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥለሴ፣ በቀጣይ በብራዚል በሚካሄደው ኮፕ 30 አፍሪካ የጋራ ድምጿን ማሰማት እንዳለባት ገልጸዋል፡፡

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #UNclimateweek #ClimateAction #AfricanClimateSummit

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: