ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ፤ ጥበብ ለመድረክ ብቻ ሳይሆን ለሀገር እድገት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የጥበብ ዘርፉን በፖሊሲ የተደገፈ ለማድረግ ረቂቅ ሰነዶች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኪነ ጥበብ ውድድሩ የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ያግዛልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙሀዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ እየተሰሩ የሚገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማጉላት ረገድ ከኪነ ጥበብ ባለሞያዎች ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ ብለዋል።
ጥበብ ለአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና የማይተካ ሚና አለው ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ከህዳሴ ግድቡ ጋር የተገናኙ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን መስራት እንደሚቻልም አንስተዋል።
በሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር ከ300 በላይ ባለተሰጥኦዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
መነሻውን ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ በማድረግ በብሄራዊ ቴአትር በሚካሄደው በዚህ ውድድር፤ የሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ በባህላዊ አልባሳት የፋሽን ውድድር፣ የስዕልና መነባነብ ስራዎች እየቀረቡበት ነው።
ውድድሩ በክልሎች ሲካሄድ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የማጠቃለያ ውድድሩ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የጥበብ ባለሞያዎች እየተሳተፉ በሚገኙበት በዚሁ ውድድር፤ የጥበብ ባለሞያዎች የየአካባቢያቸውን ባህልና ጥበብ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ውድድሩ የሚከናወነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚመረቅበት ወቅት እንደመሆኑ የጥበብ ስራዎቹ ከግድቡ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ይሆናሉ ነው የተባለው።
ዝግጅቱ ከነሀሴ 28 እሰከ 30 የሚቆይ ሲሆን "ጥበባት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በመሀሪ ዓለሙ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Art #GERD