Search

የግብርና አብዮት በአፋር

ረቡዕ ነሐሴ 28, 2017 50

የአፋር ክልል ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሃብት እና ለግብርና ምቹ የሆነ ለም መሬት ያለው ክልል እንደሆነ ይታወቃል።

የክልሉ መንግስት ከለውጡ ወዲህ ለግብርናው ዘርፍ ሰፊ ትኩረት በመስጠቱ 60 ሺህ ሄክታር የነበረውን የዘር ሽፋን ወደ 133 ሺህ ሄክታር ከፍ ማድረግ ተችሏል። 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በክልሉ የግብርና ልማት እምብርት በሆነችው አሚበራ እየተሰሩ የሚገኙ የተለያዩ የግብርና ስራዎች እየጎበኙ ይገኛሉ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል ከሀገር ውስጥ ገበያ እስከ ውጭ ገበያ በማቅረብ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

ኢንቨስተሮች በክልሉ በስፋት እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በተለይ በሙዝ ዘርፍ ምርት ማምረት ብቻ ሳይሆን ፋብሪካዎችም መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በ2018 ምርት ዘመን ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክረምት ወቅት ለመሸፈን ከታቀደው 45 ሺህ ሄክታር አሁን ላይ ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር መሸፈን ተችሏል ብለዋል።

ክልሉ ያለውን የእንስሳት ሀብት ለማሳደግ በሌማት ትሩፋት ዘርፍ በማር፣ ዶሮ እርባታ፣ የወተት እና ስጋ ዘርፍ ትልቅ መነቃቃት መፈጠሩን ርዕሰ መሰትዳድሩ ገልፀዋል።

በእንስሳት መኖ ዘርፍ፤ በሶላር የሚሰሩ መስኖ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት በተለይ በጭፍራ፣ አሳይታ፣ አፋምቦ፣ አሚበራ፣ ዱል-ኤላሳ እና ዱብቲ ወረዳዎች ሰፊ ሄክታር በእንሳት መኖ እየለመ አንደሚገኝም አንስተዋል።

አሁን ላይ በክልሉ የማይታሰቡ የነበሩ የተለያዩ የሰብል ምርቶች ማሾ፣ ሱፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ በከፊል አርሶ አደር እና ኢንቨስተሮች በስፋት እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ጠቅሰዋል።

በክልሉ አሁን ያለው የግብርና አብዮት ከምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በተጨማሪ የህዝቡን የስራ ባህል ማሳደጉን አንዲሁ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገልፀዋል።

ክልሉ ካለው ለም መሬት በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል።

በሁሴን መሀመድ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Afar #agriculture