‹‹ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት›› በሚል መሪ ቃል የ2ኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር የመክፈቻ መርሐ-ግብር በብሔራዊ ቴአትር ተካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፥ የአንድን ሀገር ሕዳሴ የሚያበስረው ኪነ-ጥበብ ነው ብለዋል።
የአውሮፓን ሕዳሴም የኪነ-ጥበብ እና የፍልስፍና ባለሙያዎች አስቀድመው ማብሰራቸውን አያይዘው ገልፀዋል።
ለአውሮፓ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ የፈጠራ ውጤቶችም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ጠቅሰው፤ የአውሮፓ ሕዳሴ ከአውሮፓ የኪነ-ጥበብ እና የፍልስፍና ሕዳሴ መነሳቱን ተናግረዋል።
ዓለም አሁን የምትጠቀምባቸው የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች አስቀድመው በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተነደፉ ስለመሆናቸውም ነው ያነሱት።
የኪነ-ጥበብ ሕዳሴን ያልጀመረ ማሕበረሰብ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ሕዳሴን ለማምጣት እንደሚቸገር ጠቁመው፤ ኪነጥበብ ዋነኛው ሥራው አዕምሮን መሥራት፣ ማነሳሳት እና ተስፋ መስጠት ነው ብለዋል።
2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ከሚታሰብ ወደ ሚጨበጥ ህልም የምትሸጋገርበት ዓመት በመሆኑ ዝም ብሎ ቁጥር ብቻ መደመር አለመሆኑን አንስተው፤ እንደ ኪነ-ጥበብ ባለሙያ አሁን ያለንበት ወቅት ከወቀሳ ወደ ሙገሳ መሸጋገሪያ ነው ብለዋል።
አባይ ለዘመናት ሲወቀስ፣ ሲተረትበት የኖረ ወንዝ ቢሆንም፤ የወቀሳው ጊዜ አብቅቶ አሁን የሙገሳ ጊዜ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታሳያቸው ጎዳናዎቿ በኪነ-ጥበብ ሥራዎች መሞላት መቻል አለባቸው ብለዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBCdotstream #ETV #Art #Competition