የሰመራ ዩኒቨርስቲ የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍሉን በቅርቡ ሕይታቸው ባለፈው አሜሪካዊ ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ስም ሰይሟል።
የዩኒቨርሲቲው የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍል ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍል ተብሎ እንዲሰየም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መወሰኑን ተከትሎ ከነሐሴ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ክፍሉ በአዲሱ ስያሜ እንደሚጠራ ተገልጿል።
ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በሚሰጡት የፍትሕ አሰጣጠጥ ሥርዓት እና የአፋር ባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት (መድአ) ትምህርት ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት የሚታወሱ እንደመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍሉን በዳኛው ስም መሰየሙን የዩኒቨርሲቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መሐመድ አሕመድ ለኢቲቪ ተናግረዋል።
"ትሁቱ ዳኛ" በሚል የሚታወቁት ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ላሳዩት ትህትና የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍሉን በስማቸው በመሰየም ተማሪዎች የእርሳቸውን ስብዕና እንዲወርሱ ለማነሳሳት ስያሜው መሰጠቱን ገልፀዋል።
ዕውቀት እና ፍትሕ ዓለም አቀፍ በመሆናቸው እኚህ አሜሪካዊ ዳኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንደነበራቸው የጠቀሰው ዩኒቨርሲቲው፤ የትምህርት ክፍሉ በእርሳቸው ስም መሰየሙ ዩኒቨርሲቲው ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሚያደርጋቸውን የትምህርት ልማት ትብብሮች ይበልጥ የሚያጠናክር ስለመሆኑም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደምም የማህበራዊ ሳይንስ እና ሥነ-ሰብ ትምህርት ክፍሉን የሉሲን ቅሪተ አካል ባገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን ስም መሰየሙ ይታወሳል።
በሁሴን መሐመድ
#EBCdotstream #ETV #SemeraUniversity #JudgeCaprio