በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተነሱትን የተለያዩ ዓይነት የስ ማጥፋት ዘመቻዎች አሸንፈን ለግድቡ የምርቃት ቀን ደርሰናል ሲሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የዲጂታል ሚዲያ ተሟጋቹ ፈሕድ መሐመድ ከኢቲቪ 57 ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ የግድቡን ግንባታ በመቃወም ከ80 በላይ በሚሆኑ ሚዲያዎቿ በግድቡ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የጀመረችው ግብፅ፤ በተለይ የአረብ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ዶክመንተሪን ጨምሮ የተለያዩ ሐሰተኛ ዘገባዎችን ታሰራጭ ነበር ብለዋል።
ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ታዲያ በራስ ተነሳሽነት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስለ ግድቡ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረው በትናንሽ ሚዲያዎች በርካታ ትላልቅ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ በዚህም ውጤታማ መሆን ተችሏል ብለዋል።
በግድቡ ዙሪያ በአረብኛ ቋንቋ ተከታታይ ሐሰተኛ ዘገባዎች ይሰሩ ስለነበር እኛም በዚሁ ቋንቋ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ሀገራችንን ማገዝ አለብን ብለን በመነሳት ስለ ግድቡ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለአረቡ ዓለም በተከታታይ በማቅረብ ጥቃትን መመከት እና የሀገራችንን ስም ማስጠራት ችለናል ብለዋል።
በተሠሩ በርካታ ሥራዎች የግብፅ ዜጎች ኢትዮጵያ ግድቡን መሥራት፣ መልማት መብቷ ነው ማለት ጀምረዋል፤ በዲጂታል ሚዲያው ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የተለያዩ የአረብ ሀገራት ዜጎችም ወደ ኢትዮጵያ በአካል መጥተው በማየት ስለ አዲስ አበባ እና ስለ ሀገሪቱ ዕድገት መስክረዋል፤ ይህ በዲጂታል ሚዲያው ላይ የተሠራው ሥራ ውጤት ነው ብለዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#EBCdotstream #GERD #digitalmedia