የኢትዮጵያ ሬድዮ በኪነ-ጥበብ ለሀገራቸው አስተዋፅዖ ካበረከቱ ባለሙያዎች መካከል መወዳጀታችንን፣ መፈቃቀራችንን፣ ማህበራዊ ሚናችንን የሚያስቀጥል ሥራ በመስራት ምቹ ሁኔታን ከፈጠሩ፤ በሙዚቃ ሥራዎቻቸው ትልቅ አሻራ ካኖሩ ባለሙያዎች መካከል አንጋፋዋ አርቲስት ገነት ማስረሻን የስቱዲዮ እንግዳው አድርጓታል።
‹‹እንኳን ለኛ ቀርቶ ለሰውም ይተርፋል
ጭስ አልባው ነዳጅ ብለው ምን ያንሰዋል›› ብላ ያቀነቀነችለትን ዓባይ የሕዳሴው ግድብ ግንባታው በተጀመረበት ወቅት ሔዳ መመልከቷን አስታውሳ፤ አሁን ከ14 ዓመታት በኋላ ግንባታው መጠናቀቁን ተከትሎ ግድቡን ለመመልከት በቦታው መገኘቷን ድምፃዊት ገነት ከኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ባደረገችው ቆይታ ገልፃለች።
ድምፃዊቷ ግንባታው በተጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ ላይ ቆማ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፏን የገለፀች ሲሆን፤ ‹‹ግድቡን በተመለከትኩበት ወቅት የተሰማኝን ስሜት ለመግለፅ ቃላት አጥረውኛል፤ ሰው ነው ወይስ ምንድነው የሰራው ብዬ እጅግ የተደነቅኩበት ተዓምር ነው›› ብላለች።
አርቲስቷ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአቅሙን ያዋጣበት፣ አብረን የቆምንለት፣ አብረን የገደብነው፤ በራሳችን መሀንዲሶች፣ በራሳቻችን አቅም በአንድነት እጃችንን ያሳረፍንበት ግዙፍ ፕሮጀክታችን የሆነው የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ "እንኳን ደስ አለን" በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBCdotstream #ETV #GERD #RenaissanceDam #ሕዳሴግድብ #genetmasresha