ኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ፣ በሕዝብ ገንዘብና የጉልበት መዋጮ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ገንብታለች። ይህ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት የሀገርን ልማትና የሕዝብን አንድነት ከማሳየቱም በላይ፣ ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አጋር በመሆን ለአብሮ ማደግ ቁርጠኝነትን ያሳያል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ምንድን ነው?
ይህ ጥያቄ የሀገርን የልማት ህልም፣ ብሔራዊ ኩራት እና ለቀጣናዊ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ግድቡ የውሃን ግጭት ሳይሆን የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት ያለመ ነው።
“ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ገድባ የግብፅን ህዝብ ልታስጠማ ነው” የሚል አስተሳሰብ መሰረት የሌለው ነው። የኢትዮጵያ አቋም ሁሌም ግልጽ እና ወዳጃዊ ነው። ዓላማው የተፈጥሮን ሀብት በመጠቀም በቂ ኤሌክትሪክ በማመንጨት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት እንዲሁም ከሌለን ላይ ለጎረቤት ሀገራት ማካፈል ነው።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለሱዳን፣ ጂቡቲ፣ እና ኬንያ ሳይቀር የጋራ ተጠቃሚነት ምሳሌ ነው። ይህ ተግባር በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ ሀገራትን ውሃ ገድቦ የመጉዳት ፍላጎት ሳይሆን፣ የፈሰሰውን ውሃ ወደ ጠቃሚ የኢነርጂ ምንጭ በመቀየር ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ያመላክታል። ሀገሪቱ ከአሁን በፊት የጀመረችው ይህ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ወደፊትም በስፋት እንደሚቀጥል በመግለጽ ለትብብር ያላትን ቁርጠኝነት ደጋግማ አረጋግጣለች።
ለአፍሪካ የኃይል ትስስር ማሳያ
የአፍሪካ ኅብረት ዋነኛ እቅዶች ከሆኑት መካከል አንዱ አህጉራዊ የኃይል መተሳሰር (Continental Power Pool) ነው። ይህ እቅድ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በአንድ ላይ ተያይዘው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚለዋወጡበት መረብ መፍጠርን ያካትታል። ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በመገንባት ለዚህ ታላቅ አህጉራዊ እቅድ ትልቁን አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች።
ግድቡ በወንዝ ፍሰት ላይ የሚሰራ በመሆኑ እና ውሃን የማያባክን በመሆኑ፣ ከውጭ ኃይል ምንጭ ነጻ የሆነ፣ ዘላቂ እና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። ይህ ኃይል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢነርጂ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ተጠቃሚ ለመሆን የምትፈልገው የራሷን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን የጎረቤቶቿን ኢነርጂ አብራ ለማሳደግ በማለም ጭምር ነው። ይህ አሰራር የግድቡን ዓላማ የጋራ ዕድገት መሆኑን ያሳያል።
ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት ነው?
የህዳሴ ግድብ ከየትኛውም የኢኮኖሚ ፕሮጀክት በላይ ለኢትዮጵያውያን ጥልቅ ትርጉም አለው። ከዚህ ውስጥ ለአብነት ያህል፦
የሉዓላዊነት እና የማንሰራርት ምልክት፦ ግድቡ በውጭ ሀገር ብድር ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያን ጥረትና መዋጮ የተገነባ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለግንባታው የሰጠው ገንዘብ፣ ጊዜ እና ጉልበት፣ ሀገርን በራስ አቅም መገንባት እንደሚቻል የሚያሳይ የቁርጠኝነት ማሳያ ነው። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ በራሷ ወንዝ ዓባይ ላይ ያለመጠቀም ኢ-ፍትሐዊ የጎንዮሽ ውሎችን በፍትሐዊ የአጠቃቀም መርህ በመቀየር ለዓለም ያስተማረችበትም ጭምር ነው። ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ላይ የበላተኛ ተመልካች መሆኗ ቀርቶ ከታላቁ ዓባይ በጥቂቱ የምትጠቀምበት አንዱ መንገድ ሆኗል። በራሷ አቅም እና በራሷ ሃብት የመጠቀም ሉዐላዊ መብቷን አስከብራለጭ
ድህነትን ለመዋጋት መሳሪያ፦ ኢትዮጵያ አሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝቧ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም። ይህ ደግሞ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርትን እና የጤና አገልግሎቶችን ዕድገት ላይ የፈጠረው እንቅፋት ቀላል አይደለም። ግድቡ በሀገር ውስጥ የኃይል አቅርቦትን የሚያሳድግ በመሆኑ የኢኮኖሚውን ዘርፍ በሙሉ ያነቃቃል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ትልቁ የዓባይ ግድብ እንዲህ መጠቀም እና ማሳካት ከቻለች የሚቀራት ሁሉ ከዚህ በታች በመሆናቸው ከድህነት ለመውጣት በብርቱ መፈለጓን ብቻ ሳይሆን እንደምትወጣ ማረጋግጫ ሰንዷም ነው።
የአንድነትና የጋራ ህልም መገለጫ፦ ኢትዮጵያውያን ህብረታቸው እና አንድነታቸው ለዓለም የተገለጠው በዓድዋ ድል ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ታሪካዊ ሁነት በኋላ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚሰባሰቡበት የወል የሆነ ጉዳያቸውን ሲፈልጉ እንጂ ሲተባበሩ አልተስተዋለም። ለዚህም ነው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ዳግማዊ ዓድዋ የሆነው። ለህዳሴው ግድብ ግንባታ፣ ከማንኛውም የፖለቲካ እና የጎሳ ልዩነት በላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተባብሯል። ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያዊያንን በአንድነት የመቆም፣ የጋራ ህልም የመኖር እና በራሳቸው አቅም ለውጥ የመፍጠር አቅም ማሳያ ነው።
የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ተራ የውሃ ቁጥጥር የማድረግ አባዜ ሳይሆን የህልውናቸውን መሰረት ለመጣል የተደረገ ትግል ነው። ለዚህም ነው ግድቡ ከተፈጥሮ ሀብት ጥቅም በመውሰድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ብልፅግና የመጓዝ ጥብቅ ፍላጎት ማሳያ የሆነው።
የኢትዮጵያ በራሷ የልማት መንገድ ላይ ስትጓዝ፣ ጎረቤቶቿንና ቀጣናውን ትታ ሳይሆን አብራ በማደግ ላይ ያለች አገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠችበት ፕሮጀክት ነው ዳግማዊ ዓድዋ።
በሰለሞን ገዳ