የሂጅራ አቆጣጠር የተጀመረው ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ስደት (ሂጅራ) ከ17 ዓመታት በኋላ፣ በኸሊፋ ዑመር ኢብኑል ኸጣብ ዘመን ነው።
ሙስሊሞች በመካከላቸው በሚጻጻፉት መልዕክቶች ላይ ትክክለኛውን ቀን ለመወሰን ችግር ገጥሟቸው በነበረበት ወቅት፣ የመፍትሔው ቁልፍ የተገኘው በኸሊፋ ዑመር ኢብኑል ኸጣብ ዘመን እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
ኸሊፋ ዑመር፣ ሰሐቦችን በመሰብሰብ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል አምነው ለዘመን መቁጠሪያ ምቹ የሆኑ ኢስላማዊ ክስተቶችን የሚያስታውሱ ሐሳቦችን አሰባሰቡ።
የቀረቡት ሐሳቦች የተለያዩ የነበሩ ሲሆን፣ አንዳንዶች የቀን አቆጣጠሩን ከነቢዩ ልደት ወይም ከነቢይነት ጅማሬ ጋር እንዲያያዝ ቢያቀርቡም፣ ኢማም ዓሊ እና ኡስማን ኢብኑ አፋን የቀን አቆጣጠሩን ከነቢዩ ስደት ጋር እንዲያያዝ ሐሳብ አቀረቡ።
በዚህም የሂጅራ የዘመን አቆጣጠር ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) ከመካ ወደ መዲና ከተጓዙበት ጊዜ ጀምሮ በይፋ እንዲጀመር ሆነ።
ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ተግባራትን እንደ ረመዷን ወር ፆም፣ ሐጅ እና የዒድ ሰላት ሌሎች መሠረታዊ ግዴታዎችን ለመፈፀም ወቅቶችን ለማወቅ ይጠቀሙበታል።
በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር በጨረቃ እንቅስቃሴ የተመሠረት ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ (354 ወይም 355 ቀናት) 29 ወይም 30 ቀናት ያሏቸው 12 ወራት ይገኛሉ።
በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር አንድ ዓመት ከግርጎሮሳዊያን የዘመን አቆጣጠር በ11/10 ቀናት ያንሳል።
በጨረቃ ወይም በሂጅራ አቆጣጠር ሙሐረም የዓመቱ መቀያየሪያ መለዋጫ የመጀመሪያ ወር ሲሆን ዙልሂጃህ የመጨረሻው 12ኛው ወር ነው።
ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) በተወለዱበት እና ባደጉበት መካ ከተማ ሰዎች ወደ እስልምና እንዲገቡ ጥሪ በማድረጋቸው እንደ ጣላት ተቆጥረው በፈጣሪ ዕርዳታ ወደ መዲና በሰላም የደረሱበት ጉዞ (ሂጅራን) መሠረት አድርጎ እንዲጀመር ተደረገ።
የታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማሞ ሐጅ ጧሃ መሐመድ ሐሩን በተለይም ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለጹት፣ የጨረቃ እንቅስቃሴን መሠረት ያደረገው የሂጅራ የጊዜ አቆጣጠር አጀማመር ታሪካዊ መነሻዎች አሉት።
በሳዑዲ ዓረቢያ በመዲና ከተማ ኢስላማዊ መንግሥት መቋቋሙን ተከትሎ መልዕክቶችን በዳብዳቤ ለማስተላለፍ በሕግ ጉዳዮች እና በትምህርት ቤቶች ቀን ለመጻፍ አማራጭ ማጣታቸውን ይገልጻሉ።
ምንም እንኳን ጨረቃን መሠረት ያደረገው አቆጣጠር በቅዱስ ቁርዓን የተደገፈ ቢሆንም በወቅቱ የሚጻፉ ዳብዳቤዎች በየትኛው ዓመት፣ በየትኛው ወር መጻፋቸውን መለየት አስቸጋሪ ነበር።
ሙስሊም ምሁራን ተሰብስበው ለዘመን መቁጠሪያ መነሻ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ይጀምራሉ።
ከብዙ ውይይት በኋላ ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) ከመካ ወደ መዲና ከተጓዙበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሆን በምሁራኑ የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ የሂጅራ የዘመን አቆጣጠር እንዲጀመር መሠረት መጣሉን ያስረዳሉ።
የሂጅራ አቆጣጠር ከ6ኛው ወይም ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) ከተዘጋጀላቸው ሴራ በአላህ ፍቃድ የወጡበት በመሆኑ በከሊፋ ዑመር ኢብኑል ኸጧብ መሪነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቀጥሏል።
የዓረቡ ዓለም ምሁራን የብዙ የእውቀት መነሻዎች መሆናቸውን የሚናገሩት ሐጅ ጧሃ፣ የሂጅራ ዘመን አቆጣጠር 12ቱ ወራት ስያሜ በወቅቱ የነበሩ አጋጣሚዎችን የሚያመለክቱ ናቸው ብለዋል።
በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር 12ቱ ወራት ሙሃረም፣ ሳፋር፣ ረቢዕ አል-አወል፣ ረቢዕ አል-ሳኒ፣ ጁማደ አል-አወል፣ ጁማደ አል-ሳኒ፣ ረጀብ፣ ሻዕባን፣ ረመዳን፣ ሸዋል፣ ዙል-ቃዕዳህ፣ ዙል-ሂጃህ ተብለው የተሰየሙት የተሰየሙበትን ጊዜ የነበረውን የአየር ሁኔታ አመላካች ናቸው ብለዋል።
ለምሳሌ ረቢዕ ማለት በልግ ማለት ሲሆን በጋ ወጥቶ ቶሎ ምርት የሚመረትበት ወቅት የሚመጣበትን ወቅት ያመላክታል ብለዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBC #ebcdotstream #hijrah #mawlid