ትናንት በቻይና ቤጂንግ ተካሂዶ በነበረው ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ ላይ ተጋብዘው ቤጂንግ ከተገኙት የሀገራት መሪዎች መካከል የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ይገኙበታል።
በቻይና የተገናኙት እነዚህ መሪዎች የሁለትዮሽ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ውይይታቸው ሲጠናቀቅ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የፀጥታ ሰዎች፣ እርሳቸው ተቀምጠውበት የነበረውን ወንበር እና በእጃቸው ነክተዋቸዋል ብለው ያሰቡትን የወንበር መደገፊያ፣ ጠረጴዛ እና ሌሎች እቃዎችን በኬሚካል ሲያፀዱ ታይተዋል።
በዚህ በከፍተኛ ሁኔታ በጥንቃቄ በተካሄደ ዱካን የማጥፋት ሥራ ሁለት የፀጥታ ሠራተኞች በስብሰባው አዳራሽ ያሉትን ነገሮች በሚገባ ካፀዱ በኋላ ኪም ጆንግ ኡን የጠጡበትን ብርጭቆ በሌላ አካል እጅ እንዳይገባ ይዘውት ሄደዋል።
ሰሜን ኮሪያ በተለያየ ጊዜያት የኪም ጆንግ ኡን አሻራ እና ዲኤንኤ ወደ ሌሎች ሀገራት የስለላ ድርጅቶች እጅ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ታደርጋለች።
ከእነዚህ መካከልም እ.አ.አ በ2019 በቪዬትናም ሃኖይ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ኪም ጆንግ ኡን የነኳቸውን እቃዎች እንዲሁም ያረፉበትን ክፍል ለሰዓታት ያፀዱ ሲሆን፣ የተኙበትን ፍራሽ እና አንሶላ እንዲወገዱ አድርገዋል።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #putin #kim #DNA #security