Search

261 ዓመታትን ያስቆጠረው የጀማው ንጉሥ መስጂድ

ሓሙስ ነሐሴ 29, 2017 46

261 ዓመታትን ያስቆጠረ እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመውሊድ በዓል የተከበረበት ታሪካዊ ቦታ መሆኑ ይነገርለታል - የጀማው ንጉሥ መስጂድ። 

ጥንታዊው ጀማ ንጉሥ መስጂጅ በተለይ በመውሊድ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ይካሄድበታል። 

መስጂዱ የሚገኘው በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ከአልብኮ ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

ጀማ ንጉሥ መስጂድ በ1756 ዓ.ም በሐጅ ሰዒድ ሙጃሂድ ተቆርቁሮ የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ በስፍራው ለመጀመሪያ ጊዜ መከበሩን የሃይማኖት መሪ የሆኑት ሙሐመድ ሷሊህ ሙሐመድ ኡስማን በተለይ ለኢቢሲ ዶትስሪም ተናግረዋል። 

ጀማ ንጉሥ በቃል ኪዳን የተመሠረተ መስጂድ መሆኑን የሚናገሩት የሃይማኖት መሪው፣ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የመውሊድ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች ዋነኛው እንደሆነ ነግረውናል።

261 ዓመታትን ያስቆጠረው እና የመውሊድ በዓል የሚከበርበት ጀማ ንጉሥ መስጂድ በጥንታዊነቱ የሚጎበኝ ጭምር ነው ብለዋል።

መውሊድ በጀማ ንጉሥ መስጂድ በሦስት የተለያዩ ቀናት እንደሚከበር ጠቁመው፣ የመጀመሪያው ቀን ‘ራምሳ’ እንደሚባል እና ዋዜማው ላይ በዱዓ፣ በምሥጋና እና በዝየራ እንደሚከበር ገልጸዋል። 

ሁለተኛው ቀን ‘አወል’ በመባል ይጠራል፤ ይህም በዓሉ የሚውልበት ቀን ሲሆን፣ በዚህ ቀን የተለያዩ ሥርዓቶች በዋናነት ደግሞ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልደት (መወሊድ) እና ታሪካቸው በስፋት እንደሚዘከር አንሥተዋል።

ሦስተኛው ደግሞ ‘ሕትሚያ’ እንደሚባል እና ምዕመኑ ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ እና ከውጭ ሀገራት ጭምሮ ቦታው ላይ ተሰባስቦ ስለሀገሩ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ዱዓ የሚያደርግበት ዕለት በመሆኑ የተጣሉ ሙስሊሞች ካሉ  እርቅ እንደሚፈፅም ያስረዳሉ። 

በበዓሉ ላይ ዜጎች ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ዕድሜ እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ሳይገድባቸው በፍቅር እና በአንድነት እንደሚያከብሩ ጠቁመው፣ ጀማ ንጉሥ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን የያዘ የቱሪዝም መዳረሻ ነውም ብለዋል።

በቢታኒያ ሲሳይ

#EBC #ebcdotstream #mawlid #መውሊድ #ጀማንጉሥ