ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በኤሮ ዓባይ የድሮን ማምረቻ ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ብልፅግና ዕውን መሆኑ ስለማይቀር ይህን ለውጥ በወታደራዊ አቅምም መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል::
እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ ሪፎርም በገቢም በወጪ ንግድም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በእንዲህ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ውስጥ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚያስችል ህልም ያላቸው ሰዎች ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ ወታደራዊ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል::
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ወታደራዊ አቅምን በቅደም ተከተል ወይም አብረው ማሳደግ ካልቻሉ ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅም ገልፀዋል::
በኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት በፊት መታጠቅ ሳይሆን የመግዛት ፈተና እንደነበረ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ገዝቶ ከመጠቀም አልፎ በራስ አቅም የማምረት አቅም ላይ መደረሱን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህልውና እና ሉዓላዊነት የሚገዳዳር አደጋ ሲመጣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጀመርነውን ብልፅግና ለማስጠበቅ የወታደራዊ አቅም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መለወጥ የማያጠራጥር ሀቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢኮኖሚ የተጀመሩ ዕድገቶችን በወታደራዊ አቅም እየደገፍን መሄድ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሚመረቱት ድሮኖች በውስን ቦታዎች የታጠሩ ሳይሆኑ ለንግድ፣ ለክትትል፣ ለኦፕሬሽን አላማ የሚውሉ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በሐይማኖት ከበደ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #AbiyAhmed #aeroabay #drone