Search

ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ማዕከል ለመሆን እየሠራች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ዓርብ ነሐሴ 30, 2017 73

አፍሪካውያን ወጣቶች ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አህጉር ለመገንባት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ 2025 በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ፈተና በተወጠረችበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ ችግሩ ኢኮኖሚያችንን፣ የኑሮ ዋስትናችንን እየፈተነ በነገ ዋስትናችን ላይም እክል እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ የበካይ ጋዝ ልቀት ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ ከ4 በመቶ  በታች ቢሆንም፤ አህጉሪቱ የከፋውን ጉዳት እያስተናገደች ስለመሆኑም አንስተዋል።

ድርቅ፣ ጎርፍ፣ እያደገ የመጣ የምግብ ዋስትና ችግር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጣ ፍልሰት የከበቡን ፈተናዎች ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን አፍሪካ ተጋላጭ ብቻ ሳትሆን ተስፋ ያላት የወጣቶች አህጉር መሆኗንም መዘንጋት አያስፈልግም ብለዋል።

ከ60 በመቶ በላይ አፍሪካውያን ከ25 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ በማንሳትም፤ የአፍሪካ ልጆች ችግር ወራሾች ብቻ ሳይሆኑ በፈጠራዎቻቸው፣ በክህሎታቸው እና በትጋታቸው መፍትሄ አመንጪዎችም ስለመሆናቸውም አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በዓለም ላይ ካሉ የደን መልሶ ማልማት ሥራዎች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ያሰልፋታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ማዕከል ለመሆን እየሠራች መሆኑን እና ታዳሽ ኃይል ለጂቡቲ፣ ለኬኒያ፣ ለሱዳን እና ለታንዛኒያ እያቀረበች ስለመሆኑም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንስተዋል።

ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስኬት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሥራ መሆኑን በመጠቆምም፤  ይህ ተግባር የአፍሪካ መንግሥታት ከወጣቶች እና ከህዝባቸው ጋር በቅንጅት ምን ያህል ማሳካት እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች በተናጠል የማይፈቱ በመሆናቸው የአፍሪካ ወጣቶችም ድምፃችሁን ከፍ ብሎ እንዲሰማ ጥምረታችሁን እና ቅንጅታችሁን አጠናክሩ ሲሉ መክረዋል።

የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ያለ እናንተ የነቃ ተሳትፎ ሊሳካ አይችልም፤ ዝምታችሁን ስበሩ፣ ታላላቅ ህልሞችን አልሙ፣ ሀሳቦቻችሁን በግልፅ አንፀባርቁ ሲሉም አሳስበዋል።

በአሸናፊ እንዳለ

#EBCdotstream #AYCA2025 #AddisAbaba #Climate Solutions #GreenDevelopment