Search

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራን በስልጠና እና በመረጃ የሚደግፍ የተደራጀ ተቋም ያስፈልጋል - ኡስታዝ ጀማል በሽር

ዓርብ ነሐሴ 30, 2017 107

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍሎ እውን ያደረገውን የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጥረት ይካሄድ በነበረበት ወቅት በርካታ ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር ኡስታዝ ጀማል በሽር ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን ትርክት ለሌላው ዓለም ለማስተጋባት ይደረግ በነበረው ጥረት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በአረብኛ ቋንቋ መረጃዎችን የማሰራጨት ሥራን ዘግይተው እንደጀመሩ ጠቅሰዋል።

የግብፅ ሚዲያዎች የረጅም ጊዜ ልምድ እንዲሁም ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው በመሆኑ በአረቡ ዓለም የሚያሳድሩት ተፅዕኖም ያንኑ ያህል እንደሆነ ጠቁመዋል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ማነስም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደነበረው ኡስታዝ ጀማል ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

የሁለቱ ወገን ተሟጋቾች ሚዲያ ላይ ውይይት ለማድረግ በሚቀርቡበት ወቅት ከግብፅ ወገን የሚቀርቡ ተወያዮች ስለሚወያዩበት ርዕሰ ጉዳይ ሙሉ መረጃ አስቀድሞ ይደርሳቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ተወያዮቹ ከመንግሥት ሙሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለጉዳዩ መናገር የሚገባቸውን እና የማይገባቸውን በደንብ አውቀው ይመጡ ነበር ነው ያሉት።

በተቃራኒው በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት እንደነበር ኡስታዝ ጀማል አያይዘው አንስተዋል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጥረት ወቅት ይገጥም የነበረው ሌላው ችግር ስለጉዳዩ ለማወያየት የሚቀርቡት ጋዜጠኞች ለግብፅ ይወግኑ የነበረ መሆኑ ነው ብለዋል።

የቋንቋ ልዩነቱን በመጠቀም በተለይ በእንግሊዘኛ አቋማቸውን ለማንፀባረቅ ይሞክሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ሀሳብ አዛብተው ማቅረብ ትልቅ ችግር እንደነበር ያስታውሳሉ። 

በአጠቃላይ ትግሉ ስለጉዳዩ በቂ መረጃ ካለው እና በደንብ ከተደራጀ አካል ጋር የነበረ መሆኑ ጉዳዩን አክብዶት ነበር ነው ያሉት።

ለወደፊቱ እንደ ሀገር የተደራጀ ተቋም በመፍጠር በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ላይ የሚሰሩ ግለሰቦችን በማሰልጠን እና የሚያስፈልጋቸውን መረጃ በመስጠት ረገድ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

#EBCdotstream #ETV #RenaissanceDam #PublicDiplomacy

በንፍታሌም እንግዳወርቅ