“በሕብረት ችለናል” በሚል ሃሳብ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ የፖናል ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ ግድቡ የዐድዋ ድልን ያለጥይት ድምፅ በአንድነት የደገምንበት ታሪክ ነው ብለዋል።
ሕዳሴ አንጡራ ሃብታችንን ይዞ ሲሄድ የነበረውን ዓባይን ከቁጭት ወደ መቻል የቀየርንበት ፕሮጀክት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በፓናል ውይይቱ 3 የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን ከጀመሩ የሚጨርሱ ናቸው የሚለውን አዲስ ታሪክ ለዓለም ያሳወቀ መሆኑን ከፅሁፍ አቅራቢዎቹ መካከል የሆኑት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ (አፍሌክስ) ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናግረዋል።
ሕዳሴ ኢትዮጵያውያን ‘ከድህነት እና ከጨለማ ጋር አንኖርም’ ብለው የገነቡት ፤ ለቀጣይ ትውልድ በኩራት የሚያወርሱት ታሪክ መሆኑንም አቶ ዛዲግ ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው ትስስርን እና ትብብርን የሚያሳድግ ነው ያሉት ደግሞ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና የውሃ ዲፕሎማሲ አማካሪ የሆኑት አቶ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ናቸው።
አፍሪካ ካላት የሃይድሮ ፓወር እምቅ አቅም 90 በመቶው ገና አልተነካም ያሉት አማካሪው፤ ሕዳሴ ግድብ ይህን መቀየር እንደሚቻል ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።
ባለፉት 7 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ከተተከሉ ችግኞች 29 በመቶ ወይም 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉት በዓባይ ተፋሰስ ላይ መሆኑን ሌላኛው ጥናት አቅራቢ የሆኑት ጌታቸው ግዛው ተናግረዋል።
ይህም በተፋሰሱ ያለውን የደን ሽፋን በ3 ሺ 300 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በማሳደግ፤ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉ አስረድተዋል።
በሞላ ዓለማየሁ