የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበረውን የኅብር ቀን እና አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሠራተኞች እና በጡረታ ለተሰናበቱ የቀድሞ አባላት የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር አከናውኗል።
በመርሐ-ግብሩ ለበዓል መዋያ የሚሆን የቁሳቁስ ሥጦታ እና የገንዘብ ድጋፍ መበርከቱን አገልግሎቱ ለአቢሲ በላከው መረጃ አስታውቋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ትናንት ሀገራቸውን እና ተቋማቸውን በትጋት እና ዋጋ በመክፈል ጭምር ያገለገሉትን እና ዛሬም እያገለገሉ የሚገኙትን ሠራተኞች መደገፍ በሀገር ደረጃ የተጀመረው የሰው ተኮር ልማት ሥራችን አካል ነው ብለዋል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተጣለበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ለተለያዩ የኅበረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ርስቱ፣ በዛሬው ዕለት የተደረገው የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብርም የዚሁ ተግባር አካል መሆኑን አመልክተዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች ከወር ደመዛቸው በማዋጣት አቅመ ደካማ እና አረጋውያን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን አቶ ርስቱ ገልጸዋል።
ይህም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን ከማኅበረሰቡ ጋር ይበልጥ ማስተሳሰሩን እና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ ዕድል መፍጠሩን አመልክተዋል።
በቀጣይም የማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፣ በተቋም ደረጃ የተሰጠንን ተልዕኮ ከመፈጸም ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የማኅበረሰብ ተኮር የድጋፍ ሥራዎች ላይ ያለን ተሳትፎ እያደገና ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ወረዳ የመሬት መንሸራተት ላጋጠማቸው ዜጎች እና ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገር የተቋሙ ሠራተኞች እና የአረጋውያንን መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በማደስና በመገንባት በኩል ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን አገልግሎቱ ለኢቢሲ በላከው መረጃ ጠቁሟል።