Search

ለዘመናት ሲታመንበት የቆየውን የዓባይ ወንዝ ታሪክ በጥናታቸው የቀየሩት ተመራማሪ

ዓርብ ነሐሴ 30, 2017 55

ጣልያናዊው ፕሮፌሰር ክላውዲዮ ፋቼና በጂኦ-ሳይንስ የጥናት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ምርምር ያደረጉ ምሁር ናቸው።
በጂኦ-ሳይንስ ዘርፍ ያዘጋጇቸው ከ300 በላይ የምርምር ውጤቶች እና ፅሁፎችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ መጽሔቶች ላይ ማሳተም ችለዋል ፕሮፌሰር ክላውዲዮ።
ለበርካታ ዩኒቨርስቲዎች እንደማጣቀሻ ሆኖ እያገለገ የሚገኝ የመሬት ቅርፊት እና የተራሮች አፈጣጠርን የሚተነትን የምርምር ፅሁፍም ከሌሎች ምሁራን ጋር ሆነው ለሕትመት አብቅተዋል።
የፕሮፌሰር ክላውዲዮ የጥናት እና የምርምር ፅሁፎች ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ በተለያዩ ወቅቶች ባቀረቧቸው ጥናቶች በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እና እውቅናዎችን አግኝተዋል።
እኚህ ምሁር ካደረጓቸው ታላላቅ የምርምር ውጤቶች መካከል ከዓመታት በፊት በላይቭ ሳይንስ መፅሄት ላይ ያሳተሙት የምርምር ውጤት ይገኝበታል።
ፕሮፌሰሩ በጂኦ-ሳይንስ ዘርፍ የታላላቅ ምሁራን እና ተመራማሪዎችን የጥናት ውጤቶች ይፋ በሚያደርገው ታዋቂው መፅሄት ላይ አቅርበውት የነበረው ጥናት ለዓመታት ሲታመንበት የቆየውን ሃሳብም ያስቀየረ ነው።
የጥናት ውጤታቸውም የዓባይ ወንዝ የዛሬ 30 ሚሊየን ዓመት ገደማ እንደተፈጠረ ያስረዳል።
የዘርፉ ምሁራን የዓባይ ወንዝ ዕድሜ እስከ ስድስት ሚሊየን ዓመታት እንደሚሆን ለዘመናት ሲያምኑበት የቆየውን መላምት የቀየረው የፕሮፌሰር ክላውዲዮ ጥናት፤ ዓባይ ከኢትዮጵያ ተራሮች መፍለቅ እና መፍሰስ የጀመረው ከ30 ሚሊየን ዓመታት በፊት እንደሆነ የሚያስረዳ ውጤት ሆኗል።
ዛሬ ታሪክ ተለውጧል ፤ ከኢትዮጵያ ተራሮች እና አለቶች እኩል ተፈጥሮ ለ30 ሚሊዮን ዓመታት ሲፈስ የኖረው ዓባይ አሁን ማረፊያ አግኝቷል።
 
በዋሲሁን ተስፋዬ