Search

ከራሱ በላይ ሀገሩን የሚያስቀድም ፅኑ ሠራዊት

ቅዳሜ ጳጉሜን 01, 2017 2929

ለደቂቃ እንኳ እረፍት ሳያምራቸው፣ የግል የሚባል ሕይወት አጣጥመው ሳይኖሩ ለኢትዮጵያ ክብር ይዋደቃሉ።

ከጀግኖች አያቶቻቸው እና አባቶቻቸው የተረከቧትን ኢትዮጵያን ከነ ክብሯ እና ነፃነቷ በተሻለ ልዕልና ለልጆቻቸው ማስተላለፍ ነው ዓላማቸው።

ሁሌም ደስታቸውን እና ስኬታቸውን የሚለኩት በኢትዮጵያ ክብር እና ልዕልና ነው። በተሰማሩባቸው ግዳጆች ሁሉ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጠብታ ውኃ ተካፍለው ግዳጃቸውን በአኩሪ ድል ይወጣሉ።

"ከራስ በላይ ለሀገር" የሚለው ፅኑ ቃላቸው ሁሌም እንደተጠበቀ ነው። በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ ለሕዝባቸው መከታ እና መኩሪያ ናቸው - የኢትዮጵያ ወታደሮች። 

"የኩሩ ሕዝቦች መኖሪያ

የኅብረብሔር ቡቃያ፤

የሰላም ተምሳሌት ዓርማ

የቀለሞች ኅብር ኢትዮጵያ።

በደም አሻራሽ አትመው

ሕዝቦች ለሰጡን አደራ፤

ለሕገመንግሥቱ ክብር

ታጥቀን ቆመናል በጋራ።"

ይላሉ የሠራዊቱን ሕዝባዊነት የሚገልጹት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር የመጀመሪያዎቹ ስንኞች።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ከታደለቻቸው "ማሕፀነ ለምለም" ካሰኟት ፀጋዎች መካከል በማንኛውም ሁኔታው ውስጥ በፅናት የሚጠብቋት ልጆች እናት መሆኗን ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መከላከያ ሠራዊቱ ዘመኑን የዋጀ ሆኖ የአባቶቹን እና የአያቶቹን አደራ በተሻለ ሁኔታ ለትውልድ ማስተላለፍ በሚችልበት መልኩ እየተዘጋጀ ይገኛል።

በፀጥታ አካላት ላይ የተደረገው ሪፎርም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ፣ ሀገር ችግር ውስጥ በገባችበት በማንኛውም ወቅት ዝግጁ የሆነ፣ እንዲሁም በመለዮው እና በዩኒፎርሙ የሚከበር እንዲሆን አድርጎታል።

ኢትዮጵያ ያለችበት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታ ልዩ ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የተረዳው አመራሩ ሠራዊቱን በቴክኖሎጂም በሥነ-ልቦናም የማዘጋጀት ሥራውን በትኩረት ሠርቷል።

ተዳክሞ የነበረው አየር ኃይል እንዲጠናከር እና ዘመናዊ መሣሪዎችን እንዲታጠቅ ተደርጓል።

ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ የልማት ዐርበኛ፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ባነሰ መሥዋዕትነት የላቀ ድል እንዲያስመዘግብ ተደርጎ እየተዘጋጀ ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን ስትራቴጂያዊ ቦታ እና የቀጣናውን ተለዋዋጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ዳግም እንዲቋቋም የተደረገው ባሕር ኃይል ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ ተደርጓል።

ሠራዊቱ የብሔር እና የጎሣ አጥር ሳይገድበው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሀገሩን እያገለገለ ይገኛል።

የኢትዮጵያን ልዕልና እውን ለማድረግ ጨለማን በጣጥሶ ለሕዝቦች ብርሃንን ለመግለጥ ውድ ሕይወቱን እየከፈለም ይገኛል።

ኢትዮጵያን የሚዞሩት ታሪካዊ ባላንጣዎቿም ይህን ክንደ ነበልባልነቱን ስለሚያውቁ ነው የሚመኙትን እና የሚፎክሩትን የማይተገብሩት።

"ሕዝብ ነው ኃያል ክንዳችን

ሰላም ልማት ነው ቋንቋችን፤

የመፈቃቀድ አንድነት

እኩልነት ነው ዜማችን።

የማንጨበጥ ነበልባል

እሳት ነን ለጠላታችን፤

ፍሙ ከርቀት ይፋጃል

ብረት ያቀልጣል ክንዳችን።"

የሚለውን የሠራዊቱን መዝሙር ያስታውሷል።

እነዚህ ስንኞች መከለከያ ሠራዊቱ በነበልባል ክንዱ የሕዝቡ የሰላም ዋስትና መሆኑን እና ሕዝቡ ደግሞ የሠራዊቱ ደጀን መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ ኢትዮጵያን ሊተናኮሉ ባሰቡ ጊዜ የሚገጥማቸው የእሳት ነበልባል ክንድ እንደሆነ ደጋግመው እንዲያስቡበት የሚያስገድዱ ናቸው።

ይህ ሠራዊት የሰላም ዘብ ነው! ለዚህም ነው ከሀገሩ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት እና በተለያዩ ወቅቶች ችግር ውስጥ ለገቡት የአፍሪካ ሀገራት አለኝታነቱን ያረጋገጠው።

ሠራዊቱ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ሁሉ ሕዝባዊነቱን እና ጀግንነቱን በተግባር ያረጋገጠ የኢትዮጵያም የአፍሪካም መከታ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትላንትም ሆነ ዛሬ ጀግንነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን በደሙ እያፀና የመጣ፣ ነገም ይህንኑ በላቀ ግዳጅ አፅንቶ የሚቀጥል እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ነው።

በለሚ ታደሰ

#etv #EBC #ebcdotstream #ፅናት #ENDF #resilience