የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ ተጀምሯል። መድረኩ በሃይማኖት አባቶች ፀሎት ነው የተጀመረው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ መድረኩን በከፈቱበት ንግግራቸው፥ "እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክ የማይዘነጋቸውን ድሎች ያስመዘገብን ነን" ብለዋል።
ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ግን የማንግባባና ግጭት የማያጣን በመሆናችን በሚገባን ልክ ወደ ፊት መራመድ አልቻልንም ብለዋል ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት በንግግራቸው።
አለመግባባታችን በየጊዜው እየሰፋ አሁንም ድረስ የዘለቀ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ነን ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ይህ ሁኔታ እንደ ሀገር የመቀጠላችንን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል ሲሉ ገልፀዋል።
አለመግባባቶቻችንን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት፤ ሙከራዎቹ በኃይል አማራጮች ላይ የተወሰኑ ስለነበሩ ከኪሳራ የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም ብለዋል።
የኃይል አማራጮች አንዱን አሸናፊ፣ ሌላውን ተሸናፊ ከማድረግ የዘለለ ሁሉንም አሸናፊ ማድረግ የማይችሉ ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ሳይገኝ እዚህ ደርሰናል ብለዋል።
ኮሚሽኑ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ጉዳዮችን በህዝባዊ ውይይት በመለየት ላይ መሆኑንም አንስተው በዚህ ሂደት በርካታ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን አክለዋል።
ዳያስፓራው በሀገሩ ጉዳይ የሚወስንበት ዕድል እንዲያገኝ ኮሚሽኑ እየሠራ መሆኑንም መግለፃቸውን በኮሚሽኑ የሚዲያ፣ ኮሙኒኬሽንና ተደራሽነት ዘርፍ አስተባባሪ ጌራ ጌታቸው ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።
#EBCdotstream #NDC #Canada #Toronto