በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት እውን የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም ትልቅ ነገር መሥራት እንደሚቻል ለአፍሪካውያን ያሳየ መሆኑን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተመራማሪው አቶ ኪራም ታደሰ ተናገሩ።
ከ86 በመቶ በላይ የናይል ውኃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ በአቅም ችግርና በኢፍትሃዊ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ጫና ውኃዋን፣ አፈሯን እና ማዕድናቷን እንዳትጠቀም ሆና ለዘመናት ኖራለች ብለዋል።
ባለፉት 14 ዓመታት ግን ኢትዮጵያውያን ያለአንዳች ልዩነት በጋራ ባካሄዱት እልህ አስጨራሽ ትግል ከዓለማችን ትላልቅ ግድቦች አንዱ ለመሆን የበቃውን ሕዳሴ ግድብን በመገንባት ታሪክ መሥራት ችለዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ እውን መሆን የቻለው ሁሉም ኢትዮጵያውንያን በሀገር ፍቅር እና "ግድቡ የእኔ ነው" በሚል የባለቤትነት ስሜት በአንድነት ቆመው ጫናዎችን በመቋቋም የሚችሉትን ሁሉ አስተዋፅዖ በማድረጋቸው ነው ብለዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ልዩ ስሜት የፈጠረ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ሀገራዊ ግንባታ እና ሌሎች ተጨማሪ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትልቅ መሠረት የጣለ ስለመሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት
#EBCdotstream #ETV #GERD #RenaissanceDam #ሕዳሴግድብ #Unveiling