Search

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሺባ ሽገሩ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ

ሰኞ ጳጉሜን 03, 2017 57

የገዢው ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆኑት ኢሺባ፣ የፓርቲያቸውን መሪ ለመሆን በሚደረገው ምርጫ እንደማይወዳደሩም ገልጸዋል።

 

ኢሺባ ይህንን ውሳኔ የወሰኑበት ምክንያት ከአሜሪካ ጋር በነበረው የንግድ ቀረጥ ድርድር ላይ የጀመሩትን ስራ ማጠናቀቃቸውን በመግለጽ ነው።

 

ከዚህ በተጨማሪም በፓርቲያቸው ውስጥ መከፋፈል እንዳይፈጠር ለመከላከል ሲሉ "አሳማሚ ውሳኔ" መውሰዳቸውን አስረድተዋል።

 

የገዢው ፓርቲ አባላት ውሳኔውን የፓርቲውን አንድነት ለመጠበቅ የተሻለው እርምጃ ብለው ሲገልጹ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የፖለቲካ ክፍተት በመፈጠሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

 

የዋጋ ግሽበት እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አዲስ መሪ መመረጥና ለችግሮቹ መፍትሄ ማምጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከያዙ ከ11 ወራት በኋላ ነው ለመልቀቅ የወሰኑት።

 

በእሳቸው የስልጣን ዘመን ፓርቲያቸው በሁለት የምርጫ ውድድሮች ሽንፈት አስተናግዷል፣ ይህም ስልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባቸው እንደነበር ኤን ኤች ኬ ዘግቧል።

 

በሰለሞን ገዳ