ከጎንደር ከተማ የተወጣጡ እንግዶች የአምቦ እና ወንጪ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የጎንደር ከተማ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና እና ወንጌላውያን እምነት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ ኅብረተሰተብ ክፍል ተወካዮች የአምቦ ከተማ የኮሪደር ልማት፣ ታሪካዊቷን የደብረ ገነት ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም፣ የወንጪና ደንዲን ኤኮ-ቱሪዝም ተመልክተዋል።
በጉብኝቱም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
በጉብኝቱም የጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌችና የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ አካላት የታሪካዊቷን ገዳም የሙዚየምና ተያያዥ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።
የጎንደር እንግዶች በታሪካዊቷ ገዳም ያደረጉት ጉብኝትም የኢትዮጵያውያን ትስስር የማይበጠስና ከጥንተ ታሪክ እንደሚመነጭ የቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሕያው ምስክር መሆኗም ተገልጿል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በዚሁ ወቅት በአምቦና ወንጪ አካባቢ ሲደርሱ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
በታሪካዊቷ የቂርቆስ ገዳም ጉብኝታቸውም በጎንደርና ወንጪ መካከል ከ400 ዓመታት በፊት በአፄ ፋሲለደስ ዘመን የተከናወነ አስደናቂ ተግባር ማየታችን አስደንቆናል ብለዋል።
በገዳሟም የኢትዮጵያውያን የትስስር ገመድ ከጥንተ ታሪክ እንደሚመነጭ የሚያሳይ ከ400 ዓመት በፊት ዐፄ ፋሲለደስ ለወንጪ ቂርቆስ የሰጡትና ስማቸው የተጻፈበትን ደወል ማግኘታቸው እጅግ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
ከአምቦ አካባቢ በተወሰደ ኖራ ዕድሳት የተደረገለት የጎንደር አብያተ መንግስት ታሪካዊ ቅርስም የጎንደርና አምቦን ታሪካዊ ትስስር የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል።
የጎንደር ቅርሶች ዕድሳትና የወንጪ ቂርቆስ ገዳም ቅርሶች ኢትዮጵያ በህዝቦቿ አንድነት የምትሰራ ሀገር መሆኗን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአምቦ፣ የወንጪና ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝምና የታሪካዊቷ ገዳም ጉብኝትም ርቀት ያልገደበው ከጥንት ታሪክ የሚመነጭ የህዝብ ለህዝብ ትሥሥርን ለማስቀጠል ትምህርት እንደሚሰጥ አንስተዋል።
በቀጣይም የጎንደርን ህዝብ በማስተባበር የታሪካዊቷን የወንጪ ቂርቆስ የሙዝየም ፕሮጀክት እና ወደብ በመገንባት ታሪክን ለልጆቻችን ማስተሳሰሪያ አሻራ እናሳርፋለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ÷ አፄ ፋሲለደስ ለወንጪ ገዳም ያበረከቱት የደወል ስጦታ የሀገርን አስተሳሳሪ ታሪክ የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል።
የጎንደር ንጉስ የነበሩት አፄ ፋሲለደስ ለወንጪ ቂርቆስ ባበረከቱት ደወል ላይ ’’የነፍስና የስጋ መድኃኒት ይሆነው ዘንድ ንጉሰ ነገስት ፋሲለደስ ለወንጪ ባሕር ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ያበረከተው ስጦታ ነው’’ ይላል ብለዋል።
ጀግናው የዐድዋ ድል ዐርበኛ ባልቻ አባ ነፍሶ ለጎንደር ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የብራና ቅዳሴ በማስጻፍ ስጦታ ማበርከታቸውንም አስታውሰዋል።
ይህም የቅደመ አያቶች የታሪክ አሻራ ኢትዮጵዊያን በብዝኅ አንድነት ላይነጣጠሉ የተጋመዱ መሆናቸውን እንደሚያሳይ አስረድተዋል።
በቀጣይም የጎንደር ከተማ ቤተ ክህነት ምዕመናንን በማስተባበር የደሴቷን ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሙዚየም ለመገንባት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አሕመዲን አብዱልቃድር፤ የአምቦና ወንጪ ጉብኝት ኢትዮጵያውያን የአስተሳሳሪ ታሪክ ባለቤት እንደሆኑ ያሳያል ብለዋል።
አፄ ፋሲለደስ ለወንጪ ገዳም ያበረከቱት ስጦታ የሚደንቅ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ በቀጣይም አስታሳሳሪ አሻራን እናስቀጥላልን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አጫሉ ገመቹ፤ በተፈጥሮ ጸጋ የበለጸገው የገበታ ለሀገር የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ እንግዶች ጉብኝትም አስደስቶናል ያሉት ከንቲባው፤ ይህም ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ አስተሳሳሪ ገመድ እንዳለን እንድንገነዘብ ያደረገ ነው ብለዋል።
የወንጪ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ጣሰው አስራት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወንጪ ኤኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ታሪካዊቷን የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም እንድትገለጥ አድርጓል ብለዋል።
ከጎንደር ከተማ የተወጣጡ እንግዶች ለሙዝየሙ መልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ለገቡት ቃል ምስጋና አቅርበዋል።
በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመሰረተች ለሚነገርላት ታሪካዊቷ የሀሮ ደብረ ገነት ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም፣ አፄ ፋስለደስ ስማቸው የተጻፈበት ደወል ከ400 ዓመታት በፊት ማበርከታቸው ተነስቷል።
የጎንደር እንግዶች የአምቦና አካባቢው ጉብኝትም በታሪክ ግማድ የተሳሰረውን የህዝብ ለህዝብ ትሥሥር ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።