ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ የአየር ንብረት ተጠቂ ብቻ ሳትሆን የመፍትሔውም አህጉር መሆኗን በአፅንዖት ተናግረዋል።
እንደ አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ሥራ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ የተመቸ ግብርና እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማንሳት የኢትዮጵያን ሥራዎች በምሳሌነት አውስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአየር ንብረት ርዳታ ወደ አየር ንብረት ኢንቨስትመንት ለውጥ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ "ክላይሜት ኢኖቬሽን ኮምፓክት" የተሠኘ በ2030 አንድ ሺህ አፍሪካ መር መፍትሔዎች የሚገኙበትን ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
አፍሪካ በታዳሽ ኃይል፣ በምግብ ዋስትና እና የሥነ ምኅዳር ጥበቃ የመምራት አቅሟንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን 2027 የኮፕ 32 ጉባዔን ለማስተናገድ ያላትን ጥያቄም ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ኢትዮጵያን እና አፍሪካን በአየር ንብረት ጥበቃ ተግባር የመሪነት ሚና የሚያጎናፅፍ ይሆናል ብለዋል።